ዜና፡ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በህግ የማስከበር ዘመቻው ‘የአማራ ጠላቶች’ ጋር ያበሩ አካላት መያዛቸውን ተናገሩአቶ ደሳለኝ ጣሰው፡ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ምንጭ፡ አሚኮ

ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በክልሉ መዲና ባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ሲሆን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው “በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከምን ጊዜም የአማራ ጠላቶች ጋር ያበሩ አካላት ተይዘዋል” ማለታቸውን አሚኮ ዘገበ።

የምክር ቤት አባላቱ የ2014 በጀት ዓመት የ11 ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸምን መሰረት አድርገው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ለተነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የጸጥታ እና የሰላም ጥያቄዎች የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

ኀላፊው በማብራሪያቸው  “ሕዝባችንም ይህ ምክር ቤትም ሊያውቀው የሚገባው ጉዳይ ጠላት አርፎ አልተኛም፤ ጠንካራ አደረጃጀት ላይ እየሠራን ነው፤ እንሠራለንም። በክልሉ በየጊዜው የሚደረጉ ትንኮሳዎችን ለመመከት የሚያስችል ኃይል እየገነባን ነው።የክተት ጥሪውን ምክንያት በማድረግ ክተቱን ተቀብለው ለሕዝባቸው ዋጋ የከፈሉ ታሪክ የማይዘነጋው ተግባር የፈጸሙ አሉ፤ ምስጋና ይገባቸዋል” በለዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም “ሚዲያው በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያው ለጠላቶቻችን መልካም መደላድል ፈጥሮ ነበር፤ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ሥርዓት ለማስያዝ ነው እየተሠራ ያለው። ሰሜን ወሎ ፣ምእራብ ጎንደር ፣ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በጠላት አሁንም ድረስ ትንኮሳዎች የሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች ናቸው።ጽንፈኛ የቅማንት ቡድን፣ የኦነግ ሸኔ እና ተከፋይ አክቲቪስቶች ክልሉን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ በክልሉ አደገኛ ተልዕኮ ይዘዋል፤ የሕግ ማስከበሩ እንዚህን አካላት ነው ሥርዓት እያስያዘ ያለው” ሲሉ ለምክር ቤቱ ማግራሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም “ከተሞቻችን የቱሪዝምና የሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ምሳሌ መኾን ሲገባቸው የጦር መሳሪያ ጋጋታ ፣የታጣቂዎች የሚዘዋወሩበት ፣ሽብር የሚፈጥሩበት፣ የዜጎች ዋስትና ፈተና ላይ የወደቀበት፣ መንግሥትም ትንሹን ኀላፊነት የመወጣት አቅም የተፈተነበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር፤ በዚህ ኹኔታ ሕግ የማስከበር ሥራ አለመሥራት አይቻልም። ለሕዝቡ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው እውቅና ፈጥረናል። ከ6 ሚሊየን በላይ ለሚኾን ሕዝብ በየደረጀው መረጃ ሰጥተናል፤ አወያይተናል፤ ሕዝቡ የሕግ የበላይነት ይከበርልን የሚል ጥያቄ ነው ያለው።በሕግ ማስከበሩ ላይ አሉባልታዎች ነበሩ፤ ይህም ሕግ እንዲከበር የማይፈልጉ አካላት ናቸው አሉባልታውን የሚያሰራጩት” ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ይህ በንዲህ እያለም ደሳለኝ ጣሰው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ”“መንግሥት ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው” የሚል የሐሰት መረጃ የሚያሰራጩትን ማረም ግድ ይል ነበር፤ሊታወቅ የሚገባው ግን በፋኖ ስም ውንብድና የሚፈጥሩ ፣ ለንጹሃን ሞት ምክንያት የኾኑ እንዳሉና ዋጋ እንዳስከፈሉ ነው” ያሉ ሲሆን በተያያዘም፣ “ለገንዘብ ብሎ ከጠላት ጋር የሚገናኝ፣ የዘረፋ የግድያ እና ሕገ ወጥ የመሳሪያ ንግድ የሚያካሂድ በፋኖ ስም የሚነግድ አካል ነው የተገኘው። በስሙ ልክ የተገኙ ፣ ለሕዝብ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ፋኖዎቻችንን እውቅና ሰጥተናል፤ እነሱም ያውቁታል። በመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ሊቃኝ የማይፈልግ የጸጥታ ኃይል ፣ክልሉ ጄኔራል፣ ኮሎኔል እንዳይኖረው የማስከዳት ሥራ እየተሠራ ነው፤ በሕግ ማስከበሩ እርምጃ የተወሰደው በእነዚህ አካላት ላይ ነው።ሀገርና ክልልን ሊያፈርሱ የሚችሉ አካላትን መታገስ የሚገባ አይደለም፤ ትክክልም አይደለም” ብለዋል።

ሃላፊው በምላሻቸው የሰጡትን ዋቢ በማድረግ ዘገባው “በሕግ ማስከበሩ የተያዙት የአማራ ሕዝብ ሞትና የክልሉ መፍረስ የሚያሳስባቸው አይደሉም። ገንዘብ ሰበሳቢ ናቸው፤ ይዘን ስናጣራ ምን ዓላማ እንደነበራቸውና ከነማን ጋር ምን እንደሚሠሩ መስማት የሚያሳዝን ነው፤ እነዚህን ሰዎች “ጀግኖች በሕግ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ” አድርጎ ማሰብም ተገቢ አይደለም። 15 የግለሰብና የመንግሥት ተሽከርካሪ በሕግ ማስከበሩ በሕገወጥ ቡድኖች ተይዘው ተገኝተዋል፤ ተመልሰዋልም። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከምን ጊዜም የአማራ ጠላቶች ጋር ያበሩ አካላት ተይዘዋል። አርሶ አደሩን፣ ነጋዴውን እና ባለሃብቱን እንስማው፤ ማኅበረሰቡን እንስማው፤ እፎይ ብሏል” ማለታቸውን አንስቷል።

በተጨማሪም ሃላፊው፣ “ዘረፋ እና ጥይት ተኩስ ቀንሷል። በክልሉ ኹሉም አካባቢዎች ሕግ ማስከበሩ አሁን ሕዝቡም አስተዳደሩም የአማራ ልዩ ኃይል እየሞተላቸው መኾኑን ተገንዝበው ድጋፍ እያደረጉ ነው። ሕዝቡ ለሰላሙ መሥራት አለበት፤ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት፤ ለጠላቶቻችን አብረው ሕዝቡን ዋጋ የሚያስከፍሉ አካላትን ማወቅና አለመተባበር አለበት፤ ለሰላምና ደኅንነቱ በአንድነት መሥራት እንዳለበት አደራ ማለት እንወዳለን” የሚሉ መልእክቶችን  የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ በንግግራቸው አስተላልፈዋል ።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.