አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2015 ዓ.ም፡- የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት በቀጣይ ወር ለመጀመር ማቀዱን የድርጅቱ የፖሊሲ ልማት ክፍል ረዳት ዳይሬክተር ቫለሪይ ጋርኒየሪ ለሮይተርስ አስታወቁ።
ተረጂዎች በመለየቱ ረገድ ሙሉ ለሙሉ በአለም የምግብ ፕሮግራም ቁጥጥር ስር የሚወሰን መሆኑን ስናረጋግጥ ወዲያውኑ እንጀምራለን ማለታቸውን ያስታወቀው የዜና አውታሩ ዘገባ በወረዳ እና በክልሎች አማካኝነት ይወሰን የነበረውን የተረጂዎች ልየታ በማስቀረት የአም የምግብ ፕሮግራም ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በራሳቸው መንገድ ተረጂዎችን በመለየት ለመወሰን የሚያስችለውን ሁኔታ እያመቻቹ መሆኑን አመላክቷል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም መርማሪዎች በተለይ በትግራይ የረድኤት ድርጅቶችን የክትትል ሂደት ዋነኛ ድክመቶችን መለየታቸውን ለዜና አውታሩ ያስታወቁት ሃላፊዋ ከሚመለከታቸው አካላት አወንታዊ ምላሽ በመገኘቱ ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በትግራይ በሚገኙ የመጠለያ ካምፖች ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ እደላ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ ነው በሚል በትግራይ አቋርጦት በነበረው የምግብ እደላ ለህጻናት እና እናቶች ይቀርብ የነበረው የተመጣጠነ ምግብ እደላ ላይ ተጽእኖ እንዳልነበረው ድርጅቱ ማስታወቁን ዘገባው አካቷል።
በኢትዮጵያ የሚያቀርቡትን የምግብ እደላ በስርቆት ምክንያት አቋርጠው የነበሩት የአለም የምግብ ፕሮግራምም ይሁን የአሜሪካ መንግስት የረድኤት ድርጅት ዩኤስኤድ በስርቆቱ ተጠቃሚ የሆነውን አካል በይፋ አለመግለጻቸውን ዘገባው አመላክቷል።
የፕሮግራሙ የፖሊሲ ልማት ክፍል ረዳት ዳይሬክተር ቫለሪይ ጋርኒየሪ በስርቆቱ ፈጻሚ ዙሪያ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው እና የምርመራ ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑን ለዜና አውታሩ መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል። አስ