ሰኔ 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦ የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺክ “የትግራይ ተወላጆች በቂ ስቃይ ደርሶባቸዋል” ብለው በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ገለጹ። ኮሚሽነሩ ይህን የተናገሩት በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ነው። በትግራይ ውስጥ “ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ አለባቸው” ብለው ትናንት ምሽት ገልጸዋል።
“እ.ኤ.አ. በ2020 የትጥቅ ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ትግራይን ለመጀመሪያ ጊዜ ትግራይን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘሁበት ወቅት፣ አንዳንድ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎችን ተመልክቻለሁ። በአብዛኛው ምግብ የያዙ መኪኖች መቀሌ እየደረሱ ነው፣ ያንን በደስታ እቀበላለሁ። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ መደረግ አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሁለት ቀን ጉብኝት ያደረጉት ኮሚሽነር ዣኔዝ በተጨማሪም ትላንት አዲስ አበባ ባለው የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ቢሮ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በትግራይ ክልል “የባንክ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገለግሎቶችን ተቋርጠው እንዲቆዩ የማድረግ ምክንያቱ አይታየኝም” በማለት አክለዋል።
“አብዛኛው በትግራይ ላይ ያለው እገዳ አሁንም አለ። የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ለተቸገሩት ሁሉ እርዳታ እንዲያደርሱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታው አስቸኳይ መሻሻል ያስፈልገዋል። ነዳጅ በጣም ያስፈልጋል፣ ለህዝቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች መመለስ አለባቸው፣ የትግራይ ተወላጆች በቂ ስቃይ ደርሶባቸዋል።” በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ዣኔዝ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር አዲስ አበባ ላይ እንዲሁም ወደ መቀለ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀ መንበር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተዋል።
ኮሚሽነሩ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ስላደረጉት ውይይት ሲናገሩ፣ “ከክልሉ ባለስልጣናት፣ በተለይም የትግራይ ተወላጆች እያጋጠሟቸው ስላለው አስከፊ ሰብአዊ ችግር፣ ግምገማቸውን በቀጥታ መስማት አስፈላጊ ነበር፣” ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይሄን ያክል ዋጋ ሊከፍሉ እንደማይገባ እና ጦርነቱ ብዙ ጉዳቶችን እንዳደረሰ የተናገሩት ኮሚሽነር ዣኔዝ ጉዳቱ ጥልቅ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን አማራ እና አፋር ክልሎችም ተጎጂ ናቸው፣ የሁንና ህበረቱ ትኩረት እየሰጠ ያለው ለትግራይ ክልል ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ተከትሎም የአውሮፓ ህበረት ገለልተኛ አይደለም በሚል ጥያቄ ይነሳበታል እና ለዚህ ምላሻችሁ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም: “የአውሮፓ ህብረት ውግንናው ለሰብዓዊ መብት መከበር ብቻ ነው፣ ጦርነቱ አፋርን እና አማራ ክልሎችን እንደጎዳም እናውቃለን፣ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረግን ነው፣ በቀጣይ በሚኖረኝ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ሁለቱን ክልሎች እጎበኛለሁ፣ የሚነሳብን የገለልተኝነት ጥያቄም ፍጹም ትክክል አይደለም“ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውንም አል አይን የዜና አውታር ዘግቧል፡፡ አስ