ዜና፡ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የሚገኙ ስምንት ቦታዎች በትግራይ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ነዋሪዎች እና ፖሊስ ገለፁ

ራያ ቆቦ ወረዳ አካባቢ

በብሩክ አለሙ

አዲስአበባ፡ሰኔ15/2014 ዓ.ም፡– በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የሚገኙ ስምንት ቦታዎች በትግራይ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ስርጭት ገለፁ፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ ከራያ ቆቦ የተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ከአላማጣና አጎራባች አካባቢዎች የተፈናቀሉ 70,000 የሚገመቱ ተፈናቃዮች በቆቦ፣ ሮቢት፣ ጎብዬና ወልዲያ ከተሞች እንዲሁም በድሌሮቃ ጃራ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓትም የትግራይ ሃይሎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የሚገኙ ስምንት አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቆጣጠራቸውን ነዋሪዎች እና ፖሊስ ገልፀዋል።

ስሙን መግለፅ ያልፈለገ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የአዲስ ቅኝ ቀበሌ ነዋሪ የትግራይ ሃይሎች ከአንድ ወር በፊት አባቱን በእርሻ ላይ እያለ እንደገደሉበት ገልፆ  “ባዘጋጀነው ባባታችን  ተስካር ላይም ሃይሎቹ መጥተው የተዘጋጀውን በልተው በሬዎችና ሌሎች እቃዎችን ዘርፈው ሄደዋል” ሲል ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ገልጿል፡፡

ሌላዋ የአዲስ ቅኝ ነዋሪ የነበረች እንደተናገረችው በተመሳሳይ መልኩ የእሷም አባት በማሳ ላይ የትግራይ ሃይሎች መገደሉንና ለተስካሩ የተዘጋጀውን ምግብ መዝረፋቸውን ተናግራለች፡፡ አክላም አምስት ወንድምና እህቶቿ የት እንደሉ የማታውቅ መሆኑንና እናትዋንም ጥላ ለመሰደድ መገደድዋን ገልፃለች፡፡

ነዋሪዎቹ በተጨማሪም እንደገለፁት የትግራይ ሃይሎች አዲስ ቅኝ፣ ጨለንቆ፣ ድንጋይ፣ ታገዳ፣ ኮባ፣ ማሃዶ ቀበሌና ሌሎች አካባቢዎችን ተቆጣጥረው መቆታቸውን ገልፀው አሁን ላይ ከቦታው ለቀው እየወጡ በመሆናቸው ቦታዎቹን ፋኖ በመተካት እየተሰማራ ነው ብለው ተናግረዋል።

የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ ቤት ኃላፊ ኮማንደር ነጋ ድንበሩ ከትግራይ ክልል የሚጎራበቱ የወረዳው ቀበሌዎች ላይ የሰበአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ መሆኑን የገለፁ ሲሆን አክለውም በአካቢዎቹ ላይ ዘረፋና ድብደባ እንዲሁም የሚኒሻና የፀጥታ ሀይሎች ቤትን ጣሪያውን እስከመገንጠል የደረሰ መብት ጥሰት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ኮማንደሩ የትግራይ ሃይሎች ከሳምንት በፊት 033 መሃጉ የሚባል ቀበሌ በመቆጣጠር ዘረፋና ውድመት ማድረሳቸውን በመግለፅ  ለዘላቂ ሰላም የሚበጅ ተግባር በፌዴራል መንግስት መፈፀም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ከህወሓት በኩል ለሰላም ማንኛውንም ጥረት እንደሚያደርጉ፣ በአንጻሩ ትግራይ ክልል ከበባ ውስጥ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ተይዘዋል ስለተባሉት ቀበሌዎችም ሆነ በአዲስ ቅኝና አካባቢዎቹ ተፈጸመ ስለተባለው የመብት ጥሰቶች እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም፡፡

በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ጦርነት መጀመሩ የሚታወስ ሲሁን በትግራይ በነበረው ጦርነት በኤርትራ ኃይሎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ ብዙ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ኋላም ይህ ጦርነት ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች በመንሰራፋቱ ለበርካታ ዜጎች ሞት፣ መፈናቀል እና መሰደድ ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ ጊዚያትም የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ይህ ለብዙዎች ፈተና የሆነን ጦርነት የፌደራል መንግስትን ጨምሮ በጦርነቱ ሲሳተፉ የነበሩትን ሃይሎች እንዲያቆሙ ሲወተውቱ እንደነበርም ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓትም የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆን ጨምሮ እነዚህ ሃይሎች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሩያ እንዲፈቱ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። አስ

 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.