አዲስ አበባ፡ ግንቦት 24/ 2014 ዓ.ም.- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ትብብር ድርጅት [Organization of Educational Cooperation (OEC)] ዋና ፀሀፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም ጋር ትናንት ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።
ባደረጉት ውይይትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት እንደሆን ጠቅሰው፤ ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ በጀት 20 በመቶው ለዘርፉ እንደሚመድብ ገልፀዋል።
አቶ ደመቀ ትምህርትን በማስፋፋት እና ተደራሽነትን በማሳደግ ብዙ ውጤት መገኘቱን የጠቀሱ ሲሆን ባሁኑ ወቅት በጥራት ላይ የሚስተዋለውን ጉድለት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለያዘችው የትምህርት ጥራትን የማሳደግ እቅድ በዘርፉ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሚንስትሩ፤ ከተቋማቱ ጋር ያላትን ትብብር ታጠናክራለችም ብለዋል።
ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም በበኩላቸው የትምህርት ትብብር ድርጅት ድርጅት ( OEC ) የትምህርት ጥራትን በማሻሻል እና የትምህርትን አካታችነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና ፀሃፊው ኢትዮጵያ በድርጅቱ ውስጥ ያላት ሚና ከፍ እንዲልና የድርጅቱን ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ላይ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀው ለዚህም ፍቃድ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም አዲስ አበባ የበርካታ አለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና የዲኘሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ለማድረግ መፈለጉን አክለው ገልፀዋል። ጥያቄው በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ታይቶ ምላሽ እንደሚሰጠው በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
የትምህርት ትብብር ድርጅት ( OEC ) በ2012 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን የሰብአዊ ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ-ሃብታዊ ልማትን ለማምጣት የተመጣጠነ የትምህርት እድገት ላይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለመስራት የተቋቋመ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።አስ