ትንታኔ: በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ ወዴት ያመራ ይሆን?

በጌታሁን ፀጋዬ

ታህሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ: በትግራይ ክልል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከስድስት ሳምንታት በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአል-ፋሻጋ ግዛት ላይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን አለመግባባት ለመፍታት መስማማታቸውን ለኢትዮጵያውያን እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ መግለጫውን የሰጡት በትግራይ ጦርነት በመቀስቀሱ በሱዳን እና ኢትዮጽያ  መካከል ዳግም ባገረሸው ውጥረት ምክንያት ሱዳን ጦሯን በአል-ፋሻጋ ግዛት (በሱዳን እና በኢትዮጵያ የሚገኝ አዋሳኝ ድንበር ሲሆን፣ በምስራቅ የአትባራ ወንዝን በደቡብ ደግሞ የተከዜ ወንዝን ያገናኛል) ላይ ለማሰማራት መወሰኗን ተከትሎ ነው። ግዛቱ 260 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ለም መሬት ነው። ቦታው በትግራይ ጦርነት እስኪጀመር ድረስ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር የነበረ ሲሆን በኢትዮጽያውያን ዘንድ ማዜጋ ተብሎ ይጠራል።

አምባሳደሩ በሰጡት መግለጫ “ጉዳዩን ለማባባስ የሞከሩት የኢትዮጵያ ጠላቶች” ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል። ነገር ግን እነዚህ ጠላቶች ስላልተሳካላቸው ሁለቱ አገሮች “ችግሮቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቃል ገብተዋል” ብለዋል። ነገር ግን ይህ ማረጋገጫ ከተሰጠ ከአንድ ዓመት በኋላ፣  የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን “የድንበር ጉዳይ በተመለከተ የሱዳን መንግስት እያሳየ  ያለውን  ጠብ-አጫሪ ባህሪ በፅኑ አወግዛለሁ” ብሏል።

“ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ፊታችንን ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ስናዞር፣ ያከበርነውን እና ዘላቂ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ለመታዘዝ የተስማማንበትን ቅድመ ሁኔታ በመጣስ ሱዳን ኢትዮጵያን ወራለች” 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን

አሁን  በሰላማዊ መንገድ እልባት ማግኘት ባይቻልም ኢትዮጵያ ክሷን በማደስ ሱዳን ኢትዮጵያን የወረረች መሆኗን ገልፃለች። ግንቦት 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማ ቀርበው ባሰሙት ንግግር፣ “ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ፊታችንን ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ስናዞር ፣ ያከበርነውን እና ዘላቂ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ለመታዘዝ የተስማማንበትን ቅድመ ሁኔታ በመጣስ ሱዳን ኢትዮጵያን ወራለች” ብለዋል።

 “ይህ ድርጊት የኢትዮጵያን ሕዝብ በእጅጉ አስቆጥቷል፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ጎድቷል፣ ብዙዎችን አፈናቅሏል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ ብዙ ጫናዎችን ያስከተለ ወረራ ነው። አካባቢውን መውረር ብቻ ሳይሆን የጂኦግራፊ እና የስነ-ህዝብን አወቃቀር  ለመለወጥ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። ይህ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ጉዳዩን አሳውቀናል“ ሲሉ አቶ ደመቀ አክለው ተናግረዋል።

ከታህሳስ 2013 እስከ ከየካቲት 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ሱዳን  አካባቢውን ለቃ እንድትወጣ ያደረገቻቸው በርካታ ሙከራዎች ምንም ውጤት ሳያመጡ ቀርተውል። የአማራ ክልል ባለስልጣናት  “የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን አስተዳደር ተቋማት አፍርሷል፣ ወታደራዊ ካምፖችን ተቆጣጥሮ ነዋሪዎቹን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ እንዲሁም ሰብልንና ንብረትን አወድሟል። ሱዳን የኃይል አጠቃቀምን እና የድንበር ማካለል ስምምነቶችን በመቃወምና የአለም አቀፍ ህግን በመጣስ አይን ያወጣ እርምጃ ወስዳለች ”ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበዋል።

ሰለ ድንበሩ ታሪካዊ ክርክሮች 

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተፈጠረው የአል-ፋሻጋ ውዝግብ የሚጀምረው በ1894 ዓ.ም. በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በቅኝ ገዥ እንግሊዝ መካከል በሱዳን የተደረገውን አከራካሪ ስምምነት ተከትሎ ነው። የስምምነቱ አውድ በሰፊው የተገለፀ ሲሆን  በእንግሊዞች በኩል  በዘፈቀደ መንገድ ድንበሩ የተከለለ ስለነበር ሁኔታው  ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል። ኢትዮጵያ አል ፋሻጋ ከ40-50 ኪሜ በምዕራብ በኩል በሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል ያለውን ድንበር የሚያዋስን ነው ስትል ሱዳን በበኩሏ አል ፋሻጋ የገዳሬፍ ግዛት አካል ነው በማለት የስምምነቱን ካርታ በማስረጃነት ታቀርባለች።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1964 ዓ.ም. የሰሜን እና ደቡብ ሱዳን ግጭት ለመፍታት ወደ ሱዳን አቀንተው የነበር ሲሆን ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ችግሮቻቸውን በሚመለከት መክረው ተመልሰዋል። የዚህ አይነት ጥረቶች የ1964ቱ አብዮት መፈንዳት ጋር ተየይዞ ተቋርጦ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ በደርግ ወታደራዊ መንግስት መመራት ከጀመረችበት  ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አገሮች በ1997 ዓ.ም በአካባቢው ላይ ሁለንተናዊ ተቀባይነት ያለው አደረጃጀት እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ  ለተከታታይ 33 ዓመታት ጠበኛ ሆነው ቆይተዋል። 

ምንም እንኳን  ስምምነቱ በይፋ ባይፀድቅም፣ በ2000 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ሱዳን፤ በፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካኝነት የመጨረሻው የድንበር ስምምነት እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች በጋራ መሬቱን ማረስ የሚችሉበት በአንፃራዊ ምቹ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።  በሁለቱም ሀገራት የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የአመራር ለውጦችን ያስከተለ ሲሆን የአል-ፋሻጋ ጉዳይም ወደ ቀድሞው ተደጋጋሚ ግጭቶች እንዲመለስ አድርጎታል። ግልጽ የሆነ የድንበር ወሰን ባለመኖሩ እና የድንበሩ ተለዋዋጭ ባህሪይ የተነሳ በሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ በዘለቀው አለመግባባትና ግጭት በአካበቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ሰለባ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ በደርግ ወታደራዊ መንግስት መመራት ከጀመረችበት  ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አገሮች በ1997 ዓ.ም በአካባቢው ላይ ሁለንተናዊ ተቀባይነት ያለው አደረጃጀት እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ  ለተከታታይ 33 ዓመታት ጠበኛ ሆነው ቆይተዋል። 

የሰሞኑ አለመረጋጋት የተፈጠረው በትግራይ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሰሞን ሲሆን ኢትዮጵያ አካባቢውን ለረጅም ጊዜ መቆጣጠር ሲሳናት የመጀመሪያ ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ሀይሎች ወደ ሱዳን ዘልቀው እንዳይገቡ እና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው እንዳይገቡ የሱዳን ባለስልጣናት ድንበሩን እንዲዘጉ መጠየቁን አምኗል። ይሁንና በርካታ ዘገባዎች እንደጠቆሙት ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ከተደረገው ስምምነት በተቃራኒው የሱዳን ገዢ ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ሌተናንት ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን በትግራይ ጦርነት ሲጀመር ከ6,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አሰማርቷል።

ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ የምዕራብ ጎንደር አስተዳደር የነበሩት እና በአሁኑ ሰዓት ግን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ጣሰው የሱዳን ሀይሎች ሰፊ መሬት በመያዝ ነዋሪዎችን እየዘረፉ እና እየገደሉ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ሃላፊው አክለውም ከ25.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመት ንብረት መዘረፉን፣ ከ400 እስከ 500 አባወራዎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም  ከሰላም በር ቀበሌ 1,750 ሰዎች መፈናቀላቸውንና መንደራቸው በእሳት መውደሙን ገልጸዋል።

የወታደራዊ ዝግጁነት ማየል

ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ሁለቱም ሀገሮች በድንበር አካባቢ ወታደራዊ ኃይል ማሰማራታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ተገንዝባለች። ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው  በኢትዮጽያ እና ሱዳን ድንበር አከባቢ አሁንም ወታደራዊ ፍጥጫ እንዳለ ከመከላከያ ሰራዊት ታማኝ የመረጃ ምንጭ አረጋግጦልናል። አካባቢው እስካሁን ድረስ በሱዳን ጦር ስር እንደሚገኝም ምንጫችን ተናግሯል።

ታህሳስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የሱዳን ሃይሎች  ግጭት ወደተከሰተበት የድንበር አካባቢ እየቀረቡ ነው ስትል ኢትዮጵያ አሳውቃለች። ከህዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ፤ ሱዳንን የኢትዮጵያ ግዛት የሆነን መሬት በመውረር፣ አስተዳደር ተቋማትን በማፍረስ፣ የጦር ካምፖችን  በመውረር፣ ነዋሪዎችን በመግደልና በማፈናቀል፣ ሰብልና ንብረትን በማውደም ጉዳት  አድርሳለች በማለት ስትከስ ቆታለች። ኢትዮጵያ ሱዳን የኃይል አጠቃቀምን እና የድንበር ማካለል ስምምነቶችን በመቃወም የአለም አቀፍ ህግን በመጣስ እርምጃ ወስዳለች ስትል የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ድርጊቱን አስተባብሏል።

“የአል-ፋሻጋ የድንበር ውዝግብ በአካባቢው የግጭት ስጋት ፈጥሯል። አሜሪካን ያሳሰባት ትልቅ ጉዳይ ነው”

የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ፀሀፊ  ሮበርት ጎዴክ

ሱዳን ትሪቡን ሰኔ 23 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው እትሙ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ፀሀፊ  ሮበርት ጎዴክ “የአል-ፋሻጋ የድንበር ውዝግብ በአካባቢው የግጭት ስጋት ፈጥሯል። አሜሪካን ያሳሰባት ትልቅ ጉዳይ ነው” ማለታቸውን ዘግቧል። አያይዘውም አስተዳደራቸው ከሱዳን እና  ከኢትዮጵያ አመራሮች ጋር በችግሩ ላይ መምከራቸውን  ገልፀው  ስምምነት ላይ እንዲደርሱም አሳስበዋል።

ጥቂት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች

የኢትዮ-ሱዳን መካከል ባለው የድንበር ውዝግብ  ሁለቱ ሀገሮች  ችግሮቻቸውን እስካልፈቱ ድረስ በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳንን አለማውገዙ ኢትዮጵያን  አሳስቧታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት “ጉዳዩን ለመፍታት ቀደም ባሉት ጊዜያት የጀመርነውን እና የፈታነውን ጉዳዮች የሚያሳዩ ሰነዶችን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት እንዲያውቁ ለማድረግ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተሰርተዋል” ብለዋል። ሆኖም ግን “ኢትዮጵያ ወደ ግጭት ላለመግባት የያዘችውን አቋም ያበረታቱ ቢሆንም፣ ሱዳን አግባብ ባልሆነ መንገድ ወረራ ስታካሂድ በግልጽ የማውገዝ አቋም ላይ ከፍተኛ ቸልተኝነት ተስተውሏል” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን

ሰኔ 2014 ዓ.ም አለም አቀፉ የቀውስ ቡድን [ International Crisis Group (ICG)] በአል ፋሻጋ ላይ ያለው ውጥረት ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት መሆኑን ገልጿል። ብዙ የውጭ ሀገራት አካላት  በሁለቱ አገሮች መካከል ጣልቃ  ለመግባት ሃሳብ ቢያቀርቡም  ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እስካሁን ግን አልተሳኩም።

አለመግባባቱን ለመፍታት የተደረጉ አንዳንድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች

ቱርክ በያዝነው አመት መስከረም ወር ላይ ሽምግልና ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ማሳወቋን ተከትሎ ጉዳዩ በሱዳን በኩል ይሁንታ አግኝቶ ነበር። “የሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃንን በዚሁ ወርሃ መስከረም ቱርክን ሲጎበኙ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ከቱርክ አመራር የቀረበላቸውን ሃሳብ ተቀብለውቷል” ሲሉ የሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አልማህዲ መናገራቸውን ሁሪየት ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል።

“የሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃንን በዚሁ ወርሃ መስከረም ቱርክን ሲጎበኙ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ከቱርክ አመራር የቀረበላቸውን ሃሳብ ተቀብለውቷል”

ማሪያም አል ሳዲቅ አልማህዲ የሱዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

በተመሳሳይ ነሃሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር  ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የሁለትዮሽ ጉዳች ላይ መክረዋል። ውጥረቱን ለመፍታት የኪር የሽምግልና ሃሳብ ከተነሱት አጀንዳዎች ዋናው እና አንደኛው ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የኪርን ሃሳብ መቀበለ ወይም አለመቀበላቸውን የሚያመላክት ፍንጭ እስካሁን የለም።

ባለፈው አመት ከሐምል 18 እስከ 20 ኢትዮጵያን የጎበኘችው የተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ዋና ፀሃፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑንም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም እንደተናገሩት ምንም እንኳን እነዚህ ጥረቶች ቢኖሩም በአል ፋሻጋ ላይ ያለው ግንኙነት በጣም ውስን ሆኖ ቆይቷል። ሃምሌ 29 ቀን፣ 2013 ዓ.ም  ሱዳን በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ መካከል ለመደራደር ላቀረበችው ጥያቄ  ቢልለኔ  ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት “ትንሽ ብልጠት ያለው” ቢሆንም በተለይ “የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቱን” ተከትሎ “የተሸረሸረውን” መተማመን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ  አጽንኦት ሰጥተውታል።

የኢትዮጵያ አቋም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ በሳለፍነው ሳምንት ለፓርላማ አባላት እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ ምንም አይነት ህግ ሳትጥስ በሰላማዊ መንገድ ጉዞዋን እንደምትቀጥል” ተናግረዋል። “ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየጣርን ነው። ኢትዮጵያ በዚህ አቅጣጫም እንድትቀጥል እየሰራን መሆኑን ማሳወቅ እንፈልጋለን” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ የምትሰነዘረው ክስ በአል-ፋሻጋ ውዝግብ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ “ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ፈጽመዋል ያሏቸውን በስደተኛ ስም የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖችን እና ሌሎች ሃይሎችን” ታስጠጋለች ሲሉ ከሰዋል።

 “መሰረታቸው ሱዳን ነው። እንደዚህ አይነት ድጋፍ መስጠት እና ለእንደዚህ አይነት ቡድኖች መሰረት መሆን ጦርነት ከመክፈት ጋር ተመጣጣኝ ነው፣ ጉዳዩንም እየተከታተልን ነው” ብለዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉንም ጥረቶች ትቀጥላለች ያሉት ሚኒስቴሩ በማንኛውም መለኪያ ግዛቱን እንደሚያሰመልሱ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የድንበር ጉዳዮችን በተገቢው መንገድ ትይዛለች ብለዋል። አምባሳደሩ “በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ላይ የሚሰሩ  የቴክኒክ ኮሚቴ፣ የፖለቲካ ኮሚቴ እና ከፍተኛ ኮሚቴ” የሚባሉ ቡድኖች መኖራቸውን  ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሱዳን ወረራ ተቀባይነት እንደሌለው ቃል አቀባዩ አስምረውበታል። ጉዳዩን ለመፍታት ሰላማዊ ድርድር ብቸኛው መፍትሄ ነው ያሉት አምባሳደሩ የሱዳንን መንገስት ”ወደ ህሊናቸው” እንዲመለሱ እና ሁኔታው እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።  ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት ያደረጓቸው ስምምነቶች እንዳሉና ኢትዮጵያ አሁን  የገጠማትን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ልትጠቀምበት እንደምትፈልግም አስረድተዋል። 

ቀጣዩ እጣ ፋንታስ?

ሁለቱም ሀገሮች ድርድር ብቸኛው ወደፊት የሚያራምድ መንገድ እንደሆነ ቢስማሙም ፤  የአልፋሽጋ መሬት ግን የራሴ ነው በማለት የይገባኛል ጥያቄን ያነሳሉ።የሱዳን ጦር ወደ አካባቢው ከገባ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፌዴራል ሃይሎች እና በአካባቢው በሚገኙ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ይፈፀማል ያለውን ወደ ግዛት የመግባት “የወረራ” ሙከራ በተደጋጋሚ እንደሚያከሽፍ ገልጿል።

በተጨማሪም ሱዳን አስፈላጊ ነው ባለች ሰዓት የመተማን አገር አቋራጭ ድንበር መክፈት እና መዝጋት፣ መፍትሄ ያላገኘው በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲሁም ኤርትራ በምስራቅ ሱዳን ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጋር ያላት ያልጠራ ተሳትፎ ፤ አለመግባባቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን እድል ውስብስብ አድርጎታል ።በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተገለጸው ሱዳን “የሽብርተኛ ቡድኖች” መደበቂያ እንደሆነች የምትናገረው ኢትዮጵያ ይባስ ብሎ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የቀጠለው ፍጥጫ ውዝግቡን አወሳስቦታል። ቀደም ሲል በሱዳን በኩል የነበረው ለኢትዮጰያ ድጋፍ የመስጠት አቋም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ መጋጨት እና በጥርጣሬ አይን ወደ መተያየት ተቀይሯል ።

 “የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳንን ወደ ሰላም ድርድር የማሳተፍ እቅድ ነድፏል፡፡እናም ጉዳዩ በሰላም ድርድርና ህግ መሰረት ይፈጸማል ”

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  

የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት በመፍታት ላይ በማቶከሩ ሱዳን አል-ፋሻጋን የኔ ነው ለማለት እድል ፈጥሮላታል። ባለፈው ወር የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አል-ሳዲቅ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ቴት  “አል-ፋሻጋ የሱዳን መሬት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

አምባሳደር ዲና “የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳንን ወደ ሰላም ድርድር የማሳተፍ እቅድ ነድፏል፡፡እናም ጉዳዩ በሰላም ድርድርና ህግ መሰረት ይፈጸማል ” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወይም የተቀረው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አይነት እቅድ እንዳላቸዉ እስካሁን ግልፅ አይደለም።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.