ዜና፡ ከሀረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ወደ አዳማ ሲጓዝ የነበረ የአምቡላንስ መኪና ቦሰት ወረዳ ላይ “በአማራ ጽንፈኞች” መቀጠሉን የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13/2014 – የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ራሳቸውን ‘ፋኖ’ ብለው በሚጠሩ ‘ጽንፈኛ የአማራ ሃይሎች’ አንድ አምቡላንስ መኪና መቃጠሉን ገልጿል። አምቡላንሱ ሚያዚያ 11 ቀን አራት ሰዎችን ጭኖ  ከምስራቅ ሀረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ወደ አዳማ ሲጓዝ እንደነበር የምስራቅ ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው በፌስቡክ ገጹ ከለሊቱ 11 ሰአት ላይ በዞኑ ቦሰት ወረዳ ሸዋ የተባለ ቦታ ላይ ታጣቂዎች አምቡላንስ በማቃጠል ከአገልግሎት ውጪ በማድረግ በሁት ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ዘግቧል። ተጎጂዎቹ ወደ አዳማ ሆስፒታል ከመወሰዳቸው ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው አልገለጸም። የዞኑን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ለተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙካራ አልተሳካም።

እነዚህ ‘ትልቅ መሳሪያ’ የታጠቁ ጽንፈኛ ሃይሎች ለግድያው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደረሰ ላለውን ዘረፋ  ተጠያቂ መሆናቸውንም ቢሮው ጠቅሷል። እነዚህ ተግባራት ለሰላምና ልማት ፈተና ሆነው ቆይተዋል ሲልም አክሏል።

ባለፉት ሳምንታት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ‘የአማራ ጽንፈኛ ቡድኖች’ ያላቸውን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሲወነጅል እንደነበር ይታወሳል። በመጋቢት ወር መጨረሻ የክልሉ መንግስት “በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሃይሎች የአማራ እና የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀንደኛ ጠላቶች” ሲል ለጠራቸው አካላት ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የዚህ አይነት ውንጀላዎች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በታጣቂ ሃይሎች እና በምስራቅ ሸዋ ዞን በፈንታሌ ወረዳ በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል ከተፈጠረ ግጭት በኋላ አይሏል። በግጭቱ የሚሊሻ አዛዡን  ኮማንደር አብዲሳ ኢፋን  ጨምሮ ከ26 ያላነሱ እና በርካታ የአካባቢ ሚሊሻዎች መገደላቸው እና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም መቁሰላቸው ይታወሳል።

በቅርቡም በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ  ከቱቱቲ ቀበሌ ወደ አፋር ክልል ሲጓዙ የነበሩ ሰባት ማዕድናትን የጫኑ  መኪናዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም እነዚሁ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸው አለበት ተብሏል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.