ዜና፡ ኦፌኮ ያገረሸው ጦርነት እንዲቆም ጠየቀ፣ አለም አቀፍ ሸምጋዮች የሰብአዊ እርቅ ጊዜውን ተጠቅመው ሰላም ለማምጣት ባለመቻላቸውና በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ትኩረት ባለመስጠታቸው መጸጸቱን ገለጸ


አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25/2014፡- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭትን በማቆም ሰላማዊ መፍትሄ እንዲሹ ጠየቀ፡፡ ኦፌኮ ክልላዊ እና አለም አቀፋዊ ሸምጋዮች የሰብአዊ እርቅ ጊዜውን ተጠቅመው ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት እና አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ማሰፈን ባለመቻላቸው እነዲሁም በኦሮሚያ ላለው ግጭት ትኩረት ባለመስጠታቸው ከፍተኛ ፀፀት እንደተሰማው ገልጿል።

ኦፌኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በመላው ኦሮሚያ የተሰፋፋውን ጦርነት ለመፍታት ቀርቶ እውቅና ሊሰጠው አለመቻሉ አሳስቦኝል ሲል የገለፀ ሲሆን በክልሉ በተለይም በግጭት እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ

ላይ ደርሷል ብሏል። አክሎም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እየተባባሰ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድርድር እንዲፈታ ሁኔታዎችንን እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል። 

ፓርቲው የግጭቶች መባባስ እና መቀጠል ህዝቡን ዳግም ለከፋ ሞት እና መፈናቀል የሚዳርግ ከመሆኑ  ባሻገር ለንብረትና መሰረተ ልማቶች ውድመት የተዳረጉ አካባቢዎችን ለበለጠ አለመረጋጋት ይዳርጋል ያለ ሲሆን እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉት በእውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ ድርድር ብቻ መሆኑ ፅኑ እምነታችን ነው ሲል አክሏል። በመሆኑም በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚ ሀይሎች ግጭቱን በማብረድ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲሹ እና በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ሁሉ ተጨማሪ ሞት እና የዜጎችን መከራ ለማሰቀረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በንቃት እና በተቀናጀ መልኩ እንዲረባረብ ኦፌኮ ጥሪውን አቅርቧል።

ኦፌኮ የኢትዮጵያ ህዝብን፣ ገዥው ፓርቲን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሚዲያ ተቋማትን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እና አክቲቪስቶች ግጭቱን ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲታቀቡ እና ችግሩን ለማርገብና ለመፍታት በአንድ ድምፅ እንዲተባበሩ ተማፅኗል። 

በመጨረሻም እየተካሄዱ ባሉት ጦርነቶች አገራችን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተጎጂ ናቸው ያለው ፓረቲው እየተባበሱ ያሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉም  የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪውን አቅርቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.