ዜና፡ ኢትዮጵያ አንበጣን ለመከላከል በተጠቀመችው ኬሚካል ሳቢያ 76 ቢሊየን የሚሆኑ የማር ንቦቿን ማጣቷን አንድ ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24/2015 ዓ.ም፡- አግሮኖሚ ጆርናል ላይ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ ኢትዮጵያ አንበጣን ለመከላከል የኬሚካል እርጭት በማከናወኗ ሳቢያ 76 ቢሊየን የሚሆኑ የማር ንቦቿን ማጣቷን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ አጋጥሞ በነበረው የአንበጣ ወረርሽኝ ሳቢያ ከፍተኛ የኬሚካል እርጭት በማካሄድ የአንበጣው መንጋ ሊያደርሰው የሚችለውን ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል ብትችልም ዳፋው በማር ንቦቿ ላይ ማረፉን ጥናቱ አስታውቋል።

በጥናቱ ላይ የቀረበው ዳታ እንደሚያሳየው ከሆነ ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ የማር ምርት 80በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፤ በገንዘብ ሲሰላ ግማሽ ቢሊየን ዶላር ይተመናል ተብሏል።

የአግሮኖሚ ጆርናል ላይ የወጣው ጥናት እንዳመላከተው ኬሚካል ርጭቱን ተከትሎ 76 ሚሊየን የሚሆኑ የማር ንቦች ሞተዋል ወይንም ደግሞ ቀፏቸውን ጥለው ጠፍተዋል። ይህም በኢትዮጵያ የማር ምርት በከፍተኛ መጠን እንዲያሽቆለቁል ዋነኛ ምክንያት ሁኗል ብሏል ጥናቱ። በኢትዮጵያ የኬሚካል ጸረተባይ ለተከታታይ ሁለት አመታት ጥቅም ላይ መዋሉን ጥናቱ ጠቁሟል።

ቲኤምጂ የተሰኘ የጥናት ተቋም ያካሄደውን ጥናት በተባባሪነት ያካሄዱት የጸረ ተባይ ቁጥጥር ስፔሻሊስቷ ኢሌና ላዙካይቲ እንደገለጹት የኬሚካል ጸረ ተባይ በፍጥነት የመከላከል አቅም ቢኖረውም በተፈጥሮ ላይ የሚኖረው ጠባሳ ግን ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፤ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በገንዘብ ቢተመን በቢሊየን ዶላር ይሆናል ብለዋል።

የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ሶማሊያ የተጠቀመችው የተፈጥሮ ጸረተባይ በመሆኑ የተሻለ ነበር ሲል የገለጸው ጥናቱ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ኬሚካል ጸረ ተባይ መጠቀም መከልክላቸው ተገቢ መሆኑን አሳይቷል ብሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.