በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 28፣ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሶስት የሰብዓዊ መብቶች መርማሪዎች እና አንድ ሹፌር በትላንትናው እለት በታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በፖሊስ መያዛቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገመቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ፡፡
መርማሪዎቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተካሄደ ባለው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች ለኢሰመጉ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አለም ባንክ አካባቢ በሄዱበት ወቅት በፖሊስ መያዘቸውንና እስካሁንም አለመፈታታቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
ባደረግነው የማጣራት ሚከራም ሰራተኞቹ እና የድርጅቱንም መኪና ጨምሮ ዓለምገና ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በፖሊስ ጣቢያው በመገኘት እንዲፈቱ ብንጠይቅም ወደ ባላይ አካላት ሂዱ የሚል ምላሽ ነው የሰጡን ብለዋል፡፡ ወደ በላይ አካላትም በመሄድ ለማነጋገር ስንሞክር የመመርመር ፍቃድ ያለው አካል እንጂ እኛ የመመርመር መብት እንደሌለን ነው የነገሩን ሲል ገልፀዋል፡፡
ኢሰመጎ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት የተቋቋመ እና በመዝገብ ቁጥር 1146 መሰረት የተመዘገበ ተቋም መሆኑን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ህጋዊ መብታችንን መጋፋት ነው ብለዋል፡፡
ኢሰመጎ ትላንት የአባላቱን መታሰር ይፋ ባደረገበት መግለጫ፣ በባለሙያዎች ላይ የተለያዩ ጫናዎች ዛቻ እና ማስፈራራትን ጨምሮ እየደረሰበት እንደሚገኝ ገልፆ የተቋቋመበትን አላማ እንዳይፈጽም እንቅፋት የሚሆን እና ባለሙያዎቹ በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ለማድረግ እና ለማሸማቀቅ የተደረገ ድርጊት ነው ብሏል፡፡
መንግስት በኢሰመጉ ላይ የተለያየ አይነት ህገ-ወጥ እስር እና የተለያዩ ጫናዎችን ከመፈጸም እንዲቆጠብ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ የኢሰመጉ ሰራተኞችን ፖሊስ በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈታ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡አስ