እለታዊ ዜና፡ የ20/80 እና 40/60 የቤት እድለኞች ከጥር አንድ ጀምሮ ውል እንደሚዋዋሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2015 ዓ.ም፡- የ14ኛ ዙር 20/80 እና 3ኛ ዙር 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቤት እድለኞች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ከጥር 1ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር በሥራ ሰዓት ባሉት 60 የሥራ ቀናት ውስጥ ባለእድለኛው ወይም ወኪሉ ቀርበው ውል መዋዋል እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስተወቀ።

የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ተፈራ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በመመሪያ ቁ/3/2011 አንቀጽ 1 እና 2 መሰረት ባለእድለኞች ወይም ወኪላቸው ምዝገባ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ባሉት 60 የሥራ ቀናት ውስጥ ቀርበው ካልተዋዋሉ ቤቱን እንዳልፈለጉት ተቆጥሮ ተመላሽ እንደሚደረግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ውል የመዋዋያ ቦታው መገናኛ በሚገኝው የቦሌ ክፍለ ከተማ ቅጥር ግቢ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ውስጥ መሆኑን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በ14 ኛ ዙር የ2080 የቤት ልማት ፕሮግራም 18 ሺ 930 ቤቶች፣ በ40/60 ደግሞ 6 ሺ 843 ቤቶች እንዲሁም ተጨማሪ 18 ስቱዲዮ ቤቶች በድምሩ 25 ሺ 791 ቤቶችን እጣ የማውጣት መርሃ ግብር በቅርቡ አካሂዷል።

የዚህ መርሃ ግብር የቤት እድለኞች ውል ለመዋዋል ሲመጡ ማሟላት የሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተዘረዘሩ ሲሆን እጣው የደረሰው ግለሰብ ውል ለመፈፀም በአካል መቅረብ፤ በውጭ የሚኖሩ ጉዳያቸውን በውክልና ለማስጨረስ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረጋግጦ (አውታንቲኬት) ሆኖ የመጣ ውክልና ማቅረብ፤ የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ ያላገባ/ች ከሆነ/ች 6 ወር ያላለፈው የምስክር ወረቀት ይዘው መቅረብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ያገባ/ች ከሆነ/ች የትዳር አጋር የታደሰ መታወቂያ ዋና እና ፎቶ 2 ኮፒ፤ የምዝገባ ማረጋገጫ (print out) ዋና እና 1 ፎቶ ኮፒ፤ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ዋና እና 1 ፎቶ ኮፒ፤ የባንክ ምዝገባ ማረጋገጫ ከተመዘገቡበት ባንክ የሚቀርብ ዋና እና 1 ፎቶ ኮፒ፤ የባንክ የቁጠባ ደብተር ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ (ፎቶ ባለው በኩል)፤ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር (TIN) ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ ቅጽ -09 (ከወረዳ ተሞልቶ ታሽጎ የሚላክ) ዋና እና 1 ፎቶ ኮፒ፤ የጠፋ ሰነድ ካለ የፖሊስ ማስረጃ ዋና እና 1 ፎቶ ኮፒ፤ 4×4 የሆነ ጉርድ ፎቶ ግራፍ 4፤ ፍቺ ካለ በፍ/ቤት የፀደቀ ፍቺ ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ የንብረት ክፍፍል ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ ባለ ዕድለኛው በሞት ከተለየ የውርስ አጣሪ ሪፖርት ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ፤ የወራሽነት ማስረጃ ዋና እና 2 ፎቶ ኮፒ ባለ እድለኛው ወይም ወኪሉ ይዞ መቅረብ እንዳለበት አቶ ጋሻው  አሳስበዋል።

ዳይሬክተሩ ከላይ የተዘረዘሩትን ቅድመ ሁኔታዎች ሳያሟላ የሚመጣ ማንኛውም ባለጉዳይ እንደማይስተናገድ ጠቅሰው፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ከላይ የተጠቀሱትን ማሟላት የግድ ሆኖ የታደሰ ፓስፖርት ወይም ቢጫ ካርድ (yellow card) የታደሰ፤ በውክልና ከሆነ የውክልና ወረቀቱ በጀርባው በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ማህተም የተረጋገጠና የተወካይ የታደሰ መታወቂያ ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሀምሌ 01 ቀን  2014 ዓ.ም ለቤት ቆጣቢዎች እጣው ወጥቶ የነበርው የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች  ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ተከትሎ በተደረገ የኦዲት ሥራ  በባንክ የተላከው እና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ያለው መሆኑንና ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች በመከሰቱ እጣው እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.