አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2/2014 ዓ.ም ፦ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጠው መግለጫ ከአንድ ወር በፊት፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.፣ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን በጥልቀት መገምገሙን አስታወሶ ባደረገው ግምገማውም “የሽብር ኃይሎችን ሁኔታ፣ ከኮንትሮባንድ፣ ከሕገ ወጥ ታጣቂዎች፣ ከጽንፈኛ የሚዲያና የፖለቲካ ቡድኖች፣ ከአክራሪ ሃይማኖተኞችና ከሙሰኞች” የሚመጡ ፈተናዎች በሀገር ላይ ያስከተሉትን ሥጋት መመልከቱን ጠቅሶ የመንግሥት መዋቅር የጥራትና የቁርጠኝነት ችግሮች እንደታዩበትና እንዲሁም “የውጭ ጠላቶቸን” ሤራና የውክልና ጦርነቱን ሁኔታ በጥልቀት መመርመሩን አስታወሷል።
ምክር ቤቱ በሚያዝያ ወር ባደረገው ስብሰባው የሕዝቡ የደኅንነት ሥጋትና ሀገራዊ አለመረጋጋት መባባሱን፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ እየተደረገ መሆኑን፤ በሃይማኖትና በብሔር አክራሪነት የተነሣ የሀገርን አንድነት ለመሸርሸር እየተሠራ መሆኑን፤ የሕገ ወጥ ታጣቂዎች ዐቅም እየጨመረ የሕጋዊ መዋቅሮች ዐቅም እየደከመ መምጣቱን፤ የሕገ ወጥ ታጣቂዎች መበራከትና መጠናከር ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ፈተና መሆኑን፤ ሕገ ወጥ ቡድኖቹ የሕዝቡን ሰብአዊና ማኅበራዊ መብቶች እየጣሱ ሕዝብ መሰቃየቱን፤ በጠቅላላ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረለት መሆኑን፤ ይህም ለውጭ ጠላቶች ዕድል እንደፈጠረላቸው፤ ነገሩ በአስቸኳይ ካልተስተካከለ ሀገርን ወደ ከፋ አደጋ እንደሚያስገባ መገምገሙን አስታውሷል።
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ “ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረኩት ስብሰባ የተከናወኑትን ተግባራት በጥልቀት ገምግሚያለው” ሲል ትናነት መግለጫ ያወጣ ሲሆን መግለጫውም “በግምገማው መሠረት የመንግሥትን ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ሕጋዊ ሥልጣን የሚገዳደሩ ኃይሎችንና የሕገ ወጥነት ተግባራትን ወደ ተገቢው ሥርዓት የማስገባቱ ሥራ በታቀደለት መንገድና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ መሆኑን፤ ሥራውም የታለመለትን ግብ እያሳካ እንደሆነ አረጋግጫለው” ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል በተከናወነው ሥራ በሺዎች የሚቆጠሩ “የሸኔ” አባላት መገደላቸውን፣ መማረካቸውንና በፈቃዳቸው እጅ መስጠታቸውን ከሪፖርቶቹ ተረጋግጧል ያለው መግለጫው አያሌ የጦር መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ከሸኔ አባላት ተማርከዋል ብሏል።
አማራ ክልልን በተመለከተም በክልሉ በተሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን ለእፎይታ ያበቁ ተግባራት መከናወናቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ መገምገሙን ገልጿል። በዚህም መሠረት ከጸጥታ ተቋማት የከዱ አባላትን በመያዝ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ተበትነው ለጸጥታ ሥጋት ሲሆኑ የቆዩ የጦር መሣሪያዎችን በማሰባሰብ፣ በሕገ ወጥ ተግባር ተሠማርተው የነበሩ አክቲቪስቶችን ሥርዓት በማስያዝ፣ ሕዝቡ የሰላምና የጸጥታው አካል እንዲሆን አወያይቶ በማሰለፍ፣ የተሻለ ሥራ መሠራቱን አክሎ ገልጿል።
በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአልሸባብ እንቅስቃሴ በጸጥታ አካላት ቅንጅት መክሸፉን የገለፀው ምክር ቤቱ አልሸባብ ከህወሀትና መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራቸው አካላት ጋር በተደጋጋሚ ሊያደርጋቸው የሞከራቸው ትሥሥሮች በተጠና የጸጥታ አካላት ኦፕሬሽን እንዲመክኑ ተደርገዋል ብላል።
ዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ የሚሞክሩ “የጥፋት ኃይሎች” በመዲናችን አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ የጥፋትና ጸጥታ የማደፍረስ እንቅስቃሴዎች መክሸፋቸውንና በዝርፊያና በከተማ ወንጀሎች ላይ ተሠማርተው የከተማውን ነዋሪዎች ሲያማርሩ የቆዩ አካላትን ተከታትሎ በሕግ ጥላ ሥር ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትም ውጤታማ ለውጥ ማምጣታቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ በመግለጫው አስፍሯል።
በመጨረሻም “በአክቲቪስትነት፣ በፖለቲካ ቡድን እና በብሔር ስም የሚደረግ ሀገር የማፍረስ ሤራን መንግሥት በምንም መልኩ እንደማይታገሥ መታወቅ አለበት” ያለው ምክር ቤቱ “ሃይማኖቶች በስማቸው ጥፋት የሚፈጽሙ ነውረኞችን መቆንጠጥ ሲገባቸው ችላ በማለታቸው ተቋማቱን እንደከለላ በመቁጠር በድርጊታቸው ቀጥለውበታል። በሀገራችን ሃይማኖት ተኮር ጥፋቶች በዘላቂነት ሊቀንሱ የሚችሉት አንዱ ወደሌላው ጣት በመቀሰር ሳይሆን ሁሉም በቅድሚያ በራሱ ተቋም ውስጥ የሚሸሸጉ ጥፋት ፈጻሚዎችን ምሽግ ለማሳጣት ሲችል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምእመናንና የሃይማኖት አባቶች የሚገባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል” ብሏል፡፡ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።አስ