ዜና: በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረው ቴዎድሮስ አስፋው በዛሬው ዕለት ከአገር መውጣቱን ቤተሰቡ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 13 / 2015 ዓ.ም፡- በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንዱ የነበረው  “ኢትዮ ሰላም” የተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል መስራች እና የፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ቴዎድሮስ አስፋው በዛሬው ዕለት ከአገር መውጣቱን ወንድሙ ቢንያም አስፋው ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፀ፡፡

ቴዎድሮስ አስፋው ከአገር ለመውጣት የተገደደው በተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰው በመሆኑና በነፃነት መስራት ባለመቻሉ መሆኑን ወንድሙ ገልጧል፡፡

ቴዎድሮስ በሚደርስበት ዛቻም የትኛውም ስቱዲዮ መስራት አለመቻሉን የገለፀው ወንድሙ “ሃሳቤን በነፃነት ወደምናገርበት ሀገር መሄድ ይሻለኛል” ብሎ ከአገር ወጥቷል ብሏል፡፡

ቴዎድሮስ አስፋው “ሁከት እና ብጥብት በማስነሳት ወንጀል” ተጠርጥሮ በእስር ለይ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን የተገኘበት መረጃ ባለመኖሩ ከአንድ ወር በፊት መለቀቁን ቢንያም ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውሷል፡፡

ቴዎድሮስ አስፋው ሚያዚያ 5፣ 2015 በፀጥታ ሀይል በቁጥጥር ስር ሲውል ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የካቲት 7 ቀን 2015 ስምንት ሰዓት አከባቢ ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ኃይሎች ተወስዶ መታሰሩን ይታወሳል። ከዘጠኝ ቀናት እስር በኋላ የካቲት 16 2015 በ30ሺ ብር ዋስትና ከእስር ተለቋል፡፡

በድጋሜ ሚያዚያ 5 በቁጥጥር ከዋለ በኋላ “በህዝብ የተመረጠን መንግስት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ” በመንቀሳቀስ፣ “በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ጥላቻን” በማሰራጨት፣ በሀገሪቷ ዕልቂት እንዲፈጸም የሃይማኖት ጉዳይን ምክንያት በማድረግ ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ሁከት እና ብጥብጥ እንዲፈጸም ሲያደርግ ቆይቷል በሚል ፖሊስ ወንጅሎት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም የአማራ ህዝብ ግፍ ደርሶበታል በማለት ያልተገባ ወሬ አሰራጭተዋል” ሲል ከጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ጋር ፖሊስ ወንጅቷቸዋል። በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው “ግላዊ ፍላጎታቸውን” ሲያንጸባርቁ ነበር የተባሉት ዳዊት እና ቴዎድሮስ፤ “የአማራን ህዝብ ለአመጽ እና ለትግል ለማነሳሳት” በሚዲያ ሲቀስቅሱ ነበር ሲል ፖሊስ በመማልከቻ ላይ አስፍሯል።  

ወንድሚ ቢንያም ቴዎድሮስ ላይ በቂ ማስረጃ በለመገኘቱ ዓቃቢ ህግ አንፈልገውም ብሎ ከአንድ ወር በፊት ተለቋል ሲል አስታውሷል፡፡ ቴዎድሮስ ወደየት አገር እንደሄድ ለደህንነቱ ሲባል አልጠቅስም ያለው ቢንያም ስለቀጣይ እቅዱ ምንም ያለን ነገር የለም ብሏል፡፡አስ

 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.