ዜና፡ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ከዘጠኝ ቀናት እስር በኋላ በ30 ሺ ብር ዋስ ከእስር ተፈታ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮ ሰላም ዩትዩብ ቻናል መስራች ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ከዘጠኝ ቀናት እስር በኋላ ትላንት ማምሻውን በ30 ሺ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱን ወንድሙ ቢንያም አስፋው ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋገጠ፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በ30 ሺ ብር ዋስትና እንዲፈታ ችሎቱ ውሳኔ የሰጠው የኢትዮ ሰላም ዩትዩብ ቻናል መስራች ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ላይ ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ነው።

ቴዎድሮስ አስፋው የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምንት ሰዓት አከባቢ ሁለት የታጠቁ እና አራት ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ሀይሎች ከቤቱ እንደወሰዱት ወንድሙ ቢንያም አስፋውን መረጃ ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወቃል። በወቅቱ የጸጥታ ሀይሎቹ ለቴዎድሮስ ያቀረቡለት ምክንያት ለጥያቄ ትፈለጋለህ የሚል ብቻ እንደነበር እና ምንም አይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዛቸውም በዘገባው ተመላክቷል።

ፍርድ ቤት ቀርቦም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የግዜ ቀጠሮ ችሎት በ30ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ብይን ሰጥቶ የነበር ቢሆን አርብ ዕለት የካቲት 10 ቀን 2015 ላይ የሚፈርም ሃላፊ የለም በሚል ሳይፈታ የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት በእስር ቤት እንዲያሳልፍ ተደርጓል፡፡ ቀጥሎም የካቲት 13፣ 2015 የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ይግባኝ በመጠየቁ ሳይፈታ የቀረው የፖለቲካ ተንታኙ ቴዎድሮስ ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበውን ይግባኝ ፍርዱ ቤቱ ውድቅ በማድረግ ትላንት የካቲት 15 ከእስር ተፈቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.