አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2015 ዓ.ም – በፃግብጂ ወረዳ በወሊድ ምክንያት 15 እናቶች፤ 5 እናቶች ደግሞ ሳይገላገሉ በመሞታቸው 15ቱ ሕፃናት ወደ ሰቆጣ መጥተው መጠለያ ጣብያ ላይ ተጠልለው እንደሚኙ የሕግና ፍትሕ አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገብያነሽ ፈንታ ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ገለጹ። ለዚህም አስቸኳይ መፍትሔ መንግሥት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ይህ የተገለፀው ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 4ተኛ ዙር 10ኛ ዓመት 24ተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ነው። ጉባኤው በህወሓት ስር የሚገኙ በአማራ ክልል ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች ነጻ የሚወጡበትን የውሳኔ አቅጣጫና ሌሎችንም ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማጽደቅ መጠናቀቁን ዞኑ በትላንትናው እለት ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የምክር ቤቱ አባላት ከአብርገሌና ከፃግብጂ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ የኀብረተሰብ ክፍሎች ምንም አይነት ድጋፍ እየደረሳቸው ባለመኾኑ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
በየቤታቸው የቀሩት የኀብረተሰብ ክፍሎችም በየቀኑ እናቶች በወሊድ ምክንያት፣ በሕክምና እና በምግብ እጦት እየሞቱ መኾናቸውንና በህውሃት ታጣቂዎችም ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በምክር ቤቱ አባላት ተገልጿል ሲል ዞኑ ጨምሮ አብራርቷል።
ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በመምከር በብሔረሰብ አስተዳደሩ አሁንም በወረራ የተያዙ አካባቢዎችን በተደረሰው ስምምነት መሠረት የፌዴራል መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥና የተፈናቀለው ሕዝብ ወደ ቀየው እንዲመልስ ጠይቋል። የዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶችም የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርሱና የተፈናቃዮችን ህይወት እንዲታደጉ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። አስ