ዜና፡ በጋምቤላ ክልል በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ የእርስ በርስ ግጭት የዘጠኝ ሰው ህይወት ሲያልፍ 17 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 17/2015 ዓ.ም፡- በጋምቤላ ክልል በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የዘጠኝ ሰው ህይወት ማለፉንና 17 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል መድረሱን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሰሞኑን በኢታንግ ልዩ ወረዳ በፒኝዋ እና ሌር ቀበሌዎች በሚኖሩ ግለሰቦች መካከል የተነሳዉ አለመግባባበት ወደ ግጭት አምርቶ በወረዳውና በጋምቤላ ከተማ መጠነኛ አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ መግለፃቸውን አስታውቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ ተከስቶ የነበረዉን የፀጥታ ችግር በክልሉና በፌዴራል የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ ስራ በቁጥጥር ስር እንዲዉል ተደርጓል ብለዋል።

ለዘመናት በአብሮነትና ወንድማማችነት ተከባብሮ የኖረውን ህዝብ ለማለያየት የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በህብረተሰቡና በፀጥታ ሀይሎች ጥረት ሴራቸው ሳይሳካ መቅረቱን ገልፀው አንድነትና ወንድማማችነት በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ የሀሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ገልፀው ከዚህ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ መንግስት እንደማይታገስ ተናግረዋል። ተከስቶ የነበረዉ የፀጥታ ችግር የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር እንዲውል ላደረጉ የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታ አካላት ምስጋናም አቅርበዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.