ዜና፡ በጋምቤላ ከተማ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ተነሳ

አቶ ኡጌቱ አዲንግ ። ምስል፡ የጋምቤላ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት

በብሩክ አለሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014:– ሰሞኑን በጋምቤላ ከተማ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መነሳቱን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በጋምቤላ ከተማ ከሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ገደቡ እስከተሳበት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደቡ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ እሰከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ማናቸውም የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት የማይቻል መሆኑንና ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ የጸጥታ ስራ ከሚሰሩና የአምቡላንስ አገልግሎት ከሚሰጡ ውጭ ማንኛውም ተሸከርካሪ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም እግረኞች 3፡00 ሰዓት ካለፈ በኋላ መንቀሳቀስ ተከልክሎ የነበር ሲሆን  ድንገተኛ ህመም ወይም መሰል ማህበራዊ ችግር ካጋጠመ በአቅራቢያው የሚገኙ የጸጥታ አካላትን በማስፈቀድ መንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

የጋምቤላ ክልል “በጋምቤላ ከተማ ባለው ነባራዊ ሁኔታ” እና “ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር” በሚል ቀደም ሲል በክልሉ ተጥሎ የነበረውን የሰዓት እላፊ አዋጅ እያጠናከረ መሆኑን   ሀሙስ ሐምሌ 8  ቀን 2014 ዓ.ም. ማስታወቁ ይታወሳል።

በወቅቱ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ እንደገለፁት በቅርቡ በጋምቤላ ከተማ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ ፕሬዝዳንት አማካኝነት የሰዓት እላፊ እገዳ ተጥሎ እንደነበር አስታውሰው  “የህብረተሰቡን ደኅንነት” ለማረጋገጥ በወጣው የሰዓት እላፊ አፈጻጸም ላይ ክፍተት አለው ብለው ነበር።

ይህ ወሳኔ  ጋምቤላ ከተማ በያዝነው አመት ሰኔ 7 ቀን የፌደራል መንግስትና የክልሉ ሃይሎች ከጋምቤላ ነጻ አውጪ ጦር  እና መንግስት ‘ሸኔ’ ብሎ በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት  የጣምራ አማፂ ሃይሎች ጋር አንድ ሙሉ ቀን በፈጀ ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ የተላለፈ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ከተማዋ ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቃም እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወቃል። 

የክልሉ መንግስት በዚያን ጊዜም የሰአት እላፊ እገዳ የጣለው  “ከከባድ ጦርነት” በኋላ “ከተማዋ ከፊል ነፃ ወጣች” ብሎ ካወጀ  በኋላ ሲሆን ጦርነቱም “በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት አድርሷል” መባሉም ይታወቃል። ነገር ግን ይህ የሰዓት እላፊ እግድ ከተላለፈ  በኋላ በተወሰደ ከባድ እርምጃ የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ እና ቤት ለቤት እየፈተሹ ከአማፂ ቡድኖቹ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ሰላማዊ ዜጎችን ሲያስሩ ታይቷል።

በተጣለውም የሰዓት እላፊ ገደብ ከአምቡላንስ እና የጸጥታ ሃይሎች ተሸከርካሪዎች በስተቀር የሰዎችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሚፈቀደው ከንጋቱ 11፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል። አቶ ኡጌቱ ሰኔ 8 ቀን በሰጡት መግለጫ አክለውም  በጋምቤላ ከተማ “ሰላማዊ ሁኔታ” እንዳለ ገልጸው የነበረ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎችም የተጠናከረ የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የጋምቤላ ከተማን ደህንነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ በተደራጀ መልክ  መረጃ ለጸጥታ ሃይሎች እንዲያደርሱ ሃላፊው ጠይቀውም እንደነበር የቅርብ ቀን ትውስታ ነው። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.