ዜና፡ በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ አተያ ቀበሌ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

የደራሼ ልዩ ወረዳ። ፎቶ: ከማህደር


አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2/2014 ዓ.ም፡- በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ አራት ሴቶችን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ የዜና አውታሩ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ንፁኃን ነዋሪዎችን መግደላቸውን ሲናገሩ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ፣ ‹‹ዕርምጃ የወሰድኩት በታጣቂዎች ላይ ነው፤›› ብሏል፡፡

በወረዳው የሚገኘው ጊዶሌ ሆስፒታል አራት ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸው ለሕክምና ከመጡ በኋላ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ሰባት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል ሲል ሪፖረተር ዘግቧል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. እና በማግሥቱ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በልዩ ወረዳው በሚገኙት አተያና ሆልቴ ቀበሌዎች ነው፡፡ የአካባቢ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ሰኞ ዕለት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ወደ ቀበሌዎች በመግባት፣ በነዋሪዎች ቤት ላይ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ በወሰዱት ዕርምጃ የነዋሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡

አቶ አልታዬ በላቸው የተባሉ ነዋሪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዕለቱ ሌሊት ከሰባት ሰዓት በኋላ በተፈጸመው ድርጊት እናቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን  ተገድለዋል፡፡ ‹‹እርሻ ላይ ውሎ የነበረው ገበሬ ቤት ሁሉ በሌሊት በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ተዘርፏል፤›› ሲሉም ድርጊቱን አስረድተዋል፡፡

አቶ እንግዳ ኪታንቦ የተባሉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በልዩ ወረዳው አተያ ቀበሌ ከተገደሉት ስምንት ሰዎች መካከል ወ/ሮ ኩንፋዴ ኩዮ የተባለች ነፍሰ ጡር ሴት መገደሏን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በነጋታው በሆልቴ ቀበሌ መልካሙ ሩቃ የተባለ አርሶ አደርን ገድለዋል፡፡ ስንቁን ይዞ ወደ እርሻ እየሄደ ነው የገደሉት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደራሼ ሕዝብ ተወካይና የሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ በተመሳሳይ ከአሥር በላይ የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤት አባሉ በዚህ ግድያ ነፍሰ ጡር እናትና ሕፃናት ጭምር ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡

የደራሼ ልዩ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ጊዶሌ ከተማ በሚገኘው ጊዶሌ ሆስፒታል የሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታደመ እንዳስረዱት፣ ሆስፒታሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ በአጠቃላይ አራት ሰዎችን ለሕክምና ተቀብሏል፡፡ ረዕቡ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ አንዲት የ26 ዓመት ሴትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ እርምጃ የተወሰደው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሳሆን በታጠቁና የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር መሆኑንና የሟቾቹም ቁጥር አራት መሆናቸውን ተናግረው ሌሎች ሃያ ታጣቂዎችን ከነትጥቃቸው መያዛቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ገልፀዋል። አክለውም በእነዚህ የታጠቁ ሃይሎች ትጣቃቸውን እስኪፈቱና ከጫካ ወጥተው ከህብረተሰቡ ጋር እስኪቀላቀሉ ድረስ  እርምጃ መውሰዳችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር፣ ክላስተር አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ ለሪፖርተር እንደገለፁት በአካባቢው የሚገኙ ታጣቂዎች በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የልዩ ወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ 72 የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ግድያ ፈጸመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በልዩ ወረዳው የሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች መንግሥት አልባ ሆነው መቀጠላቸውን አክለዋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ ላለፉት በርካታ ሳምንታት በኮንሶ እና አካባቢው ስላለው የጸጥታ ችግር ሲዘግብ መቆየቱ የታወቃል። በሚያዚያ ወር የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጆበርና አሰፋ በታጣቂዎች መገደላቸው አዲስ ስታንዳርደ ዘግቧል። በአካባቢው የመንግስት ከፍተኛ አመራር ላይ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በመጋቢት ወር በኮንሶ ዞን  በሰገን ወረዳ ዙሪያ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረሙ ገለቦ ከጓደኞቻቸው ጋር በአንድ ሆቴል ውስጥ ሲመገቡ በጥይት ተገድለዋል። የወረዳው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ካሮ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከአካባቢው ባለስልጣን ግድያ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በሚያዝያ ወር አጋማሽ በዞኑ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት ለአዲስ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ከ10 ቀበሌዎች ወደ 19,000 የሚጠጉ ሴቶችና ልጃ ገረዶችን ጨምሮ 37,000 የሚደርሱ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በኮንሶ እና ደራሼ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰገን ዙሪያ ወረዳ ከ32,000 በላይ እና በካራት ዙሪያ ወረዳ ፉቹቻ ቀበሌ ከ3 ሺ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል። በቦርቃራ፣ መታራጊዛባ ቀበሌዎች በተፈጠረው ሁከት ባለፉት ሳምንታት ብቻ ከ1,000 በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት በኮንሶ ዞን የዜጎችን ህይወት የቀጠፉ ግጭቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል። በአጎራባች ኮልሜ ክላስተር ቀበሌዎች የሰላም ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጉዳታ ኩታኖ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት እነዚህ ግጭቶች የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሞትና መፈናቀልን አስከትሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.