አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2014 ዓ.ም፡- በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላይ በተደረገ የግድያ ሙከራ አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸው እና ሌሎች አራት ሰዎች መቁሰላቸውን በሥፍራው የነበሩ የአይን አማኖችን ዋቢ አድረጎ ዶቼ ቬለ ዘግቧል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ የግድያ ሙከራው የተቃጣባቸው በአማሮ ልዩ ወረዳ በኮሬ ብሄር አባላት ላይ ይፈጸማል የተባለውን የዘር ተኮር ጥቃት ለማጣራት ወደ ልዩ ወረዳው ባመሩበት ወቅት ነበር፡፡ የግድያ ሙከራው በተደረገበት የዶርባዴ ቀበሌ ነዋሪ ነኝ ያሉ አንድ አይን አማኝ ጥቃቱ ትናንት ከቀትር በኋላ የተፈጸመው በቀበሌው መልካ ኦዳ በተባለ መንደር ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፌዴራሉ መንግሥት የተላከው አጣሪ ኮሚቴ የጥቃቱ ሰለባዎችን ለማነጋገር ወደ መንደሩ ለመግባት በተቃረበበት ወቅት ነዋሪው ተሰብስቦ ሲጠባበቅ እንደነበር የጠቀሱት አይን አማኙ “በመሀል ግን የኮሚቴው አባላት ወደ መንድሩ ሊደርሱ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንደቀሯቸው ከኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን አቅጣጫ የመጡ ታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ በመክፈታቸው የኮሚቴው አባላቱ ወደ ኋላ የተመለሱ ሲሆን ተሰብስበው ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል አምስት ሰዎች በጥይት ተመተው ወዲያውኑ ሞተዋል፡፡ በጥቃቱ የቆሰሉ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ወደ ጤና ተቋማት ተወስደዋል” ሲሉ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት የአማሮ ልዩ ወረዳ ተመራጭ የሆኑት ዶክተር አወቀ ሀምዛዬ ኮሚቴው በታጣቂ ቡድኑ በገጠመው ችግር ለጊዜው የማጣራት ሥራውን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
የልዩ ወረዳው ኮሙኑኬሽን ትላንት ባወጣው አጭር መግለጫ በዶርባዴ ቀበሌ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በፈጸመዉ የደፈጣ ጥቃት አምስት አርሶ አደሮችን በመግደል ሶስቱን አቁስሏል እንዲሁም ንብረት ዘርፏል ሲል ገልጿል።
የአማሮ ልዩ ወረዳ ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ሁለም የአከባቢው ማህበረሰብ በየደረጃዉ ከሚገኙ የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት አከባቢዉን በንቃት መጠበቅም አለባቸዉ በማለት አሳስበዋል። አክለውም የፈደራሉ መንግሥት ከኦሮሚያ መንግሥት ጋር በቅንጅት በመሥራት በአጎራባች ምዕራብ ጉጅ ዞን የተጀመረዉ የሠላም ማስከበር ሥራ በአማሮ በኩል በመሥራት የአከባቢዉን ሠላም ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸዉም ጠይቀዋል።
በአማሮ ልዩ ወረዳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች እስከ አሁን ከ200 በላይ ነዋሪዎች ሲገደሉ 50 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ መፈናቀላቸው ከልዩ ወረዳው መስተዳድር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት የልዩ ወረዳው የብልፅግና ጽህፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ ስድስት አመራሮችና ባለሙያዎች በታጠቁ ቡድኖች መገደላቸው ይታወሳል፡፡ በሁለቱ ክልላዊ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ በተደጋጋሚ ለሚፈጸመው ጥቃት መንግሥት ሸኔ ሲል የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጣቸው መግለጫዎች በመንግሥት የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች እያስተባበለ ይገኛል፡፡ አስ