አዲስ አበባ፣ መጋቢት 01፣ 2015 – በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከፃግብጅ እና አበርገሌ ወረዳዎች ተፈናቅለው በዞኑ በወለህ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ ምንም ዓይነት እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸዉን ገልጸው መንግስት ወደ አካባቢያችን እንዲመልሳቸው ጠየቁ።
ተፈናቃዮቹ ሁሉም በተስፋ ሲጠባበቀው የነበረው በትግራይ ሃይሎችና በፌዴራሉ መንግስት ስምምነት መሰረት አካባቢያቸው ሰላም ሆኖ ከነገ ዛሬ እንመለሳለን በሚል በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ቢሆንም ወደ ቄያቸው መመለስ አለመቻላቸዉን የዋግህምራ ኮሚንኬሽን ዘግቧል።
ከፃግብጅ ወረዳ የመጡት አቶ አብርሃ ወልዱ የአምስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር ላይ እንዳሉ ሲናገሩ “ዛሬ እንሞት ይሆን ነገ እንሞት ይሆን እያልን በስቃላይ ላይ እንገኛለን” ይላሉ።
ከዚህ በፊት በሴፍቲኔት ታቅፈው ይረዱ እንደነበርና ከሰኔ ወር ጀምሮ ግን የሴፍቲኔት እርዳታ እንዳልተሰጣቸው አቶ አብርሃ አክለው ገልጸዋል።
“ከፃግብጅ ወረዳ ተፈናቅለን ከመጣን ከአንድ አመት በላይ ሁኖናል ኑሮአችን ችግራችን በጣም ከፍቷል” የሚሉት ሌላኛዉ ተፈናቃይ የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ደባሽ በላይ አየለ በበኩላቸው ወደ አካባቢያችን መግባት እንፈልጋለን ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በቂ በሚባል ደረጃ እርዳታ እየቀረበላቸው አይደለም፤ ይህንን ጉዳይ ለመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ያለማቋረጥ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አልተገኘም ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ገልጿል።
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ ለመመለስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በሁለቱ ወረዳዎች ውስጥ ያለው በተለያዬ ምክኒያት ያልተፈናቀለው ህዝብም ችግር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በመጠለያና ከመጠለያ ውጭ ከ67 ሺ በላይ ተፈናቃይ ህዝብ እንደሚገኝ ከዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ያተገኘ መረጃ ያሳያል።
ቀደም ሲልም በዞኑ ከሁለት አመት በላይ በድንኳን ውስጥ የቆዩ ተፈናቃዮች ለከፋ ርሃብና በሽታ መጋለጣቸውን እንዲሁም በፌዴራል መንግስትና በህወሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የነበረው አውዳሚ ጦርነት ቢቆምም በዋግኽምራ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ አከባቢያቸው እየተመለሱ እንዳልኾነ፤ ይልቁንም ተጨማሪ ተፈናቃዮች ወደ መጠለያው እየገቡ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳር መግለፁ ይታወሳል። አስ