ዜና፡አምነስቲ መንግስት ለአንድ ወር ያክል በተመረጡ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዴዎች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ ጠየቀ

መንግስት ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቱዩብ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዴዎችን ዜጎቹ እንዳይጠቀሙ ገደብ ከጣለ አንድ ወር ሆኖታል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30/ 2015 .ም፡– የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ወር በፊት በተመረጡ የሶሻል ሚዲያ የትስስር ዘዴዎች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ የሚጠይቁ አካላት እየተበራከቱ መጥተዋል። በዛሬው ዕለትም የካቲት 30 ቀን 2015 አለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ በመጠየቅ ጎራውን ተቀላቅሏል።

በተመረጡ የማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ዘዴዎች ላይ የኢንተርኔት ገደብ የተጣለው በተያዘው አመት ባለፈው ጥር ወር መገባደጃ በመንግስት እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርትቲያን መካከል በተፈጠረ እሰጥ አገባ መሆኑ ይታወሳል።

ገደቡ ከተጣለ ሁለተኛ ወሩን ጀምሯል። ከሁለት ሳምንት በፊት መንግስት ገደቡን እንዲያነሳ ተመሳሳይ ጥሪ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሃላፊው ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በኩል ሲሆን ሌላኛው ተቋም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ደግሞ ከቀናት በፊት ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቁ ይታወሳል። ምክር ቤቱ መንግስት የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ዘዴዎችን መገደቡ እንደሚያሳስበው በመግለጽ በተደጋጋሚ ከሚጥለው ገደብ እንዲቆጠብ ጠይቋል።

መንግስት ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቱዩብ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዴዎችን ዜጎቹ እንዳይጠቀሙ ገደብ ከጣለ አንድ ወር እንደሆነው ያወሳው አምነስቲ ይህም የሀገሪቱ ባለስልጣናት ሰዎች ያላቸውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ገድበዋል፤ ይህም መረጃ የመፈለግ፣ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብትን ያካተተ ክልከላ ነው ሲሉ የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ሃላፊ ፍላቭያ ምዋንጎቭያ መናገራቸውን አስታውቋል።

የተመረጡ የማህበራዊ ትስስር ዘዴዎችን መዝጋት የዜጎችን የመናገር እና መረጃ የማግኘት መብትን በግልጽ የጣሰነው ያሉት ሃላፊዋ በተጨማሪም በሀገሪቱ ህገመንግስት እና ህጎች የተቀመጡ እንዲሁም በቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ስምምነቶች ላይ የተካተቱ መብቶችን የተቃረነ ነው ሲሉ ተችተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ ከሚወተውቱ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት አንዱ ሲሆን መንግስት ያለምንም መዘግየት ገደቡን እንዲያነሳ እና የዚህ አይነቱን ገደብ የመጣል ባህል እንዲያቆም ዛሬም አሳስቧል።

የኢንተርኔት ተደራሽነት እንዲስፋፋ ከሚሟገቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው አክሰስ ናው የተሰኘ ተቋም በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋቢ በጸጥታ ችግር ስጋት በሚል ምክንያት በተደጋጋሚ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ማድረጉን ገልጾ ተግባሩ ውጥረትን ከማስፈን ባለፈ ዜጎች መሰረታዊ መብቶቻቸውን እንዳይተገብሩ እንቅፋተ መፍጠሩን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 17ኛው የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከህዳር 19-23 ቀን 2015 ዓ.ም “የማይበገር ኢንተርኔት ለዘላ የጋራ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ መካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱ በርካ ዘገባዎች በትግራይ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ለረጅም ግዜ በተቋረጠበትና በወቅቱ ተቋርጦ የነበረው ኢንተርኔት ባልተጀመረበት ሁኔታ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሰላት ትችት ማስተናገዱ ይታወሳል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.