አዲስ አበባ፣ ጥር 17/ 2015 ዓ.ም፡– ከሁለት አመት በላይ በድንኳን ውስጥ የቆዩ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳና ፃግብጂ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፋ ርሃብና በሽታ መጋለጣቸውን የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ገለፀ።
በፌደዴራል መንግስትና በህወሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የነበረው አውዳሚ ጦርነት ቢቆምም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌ ወረዳና የፃግብጂ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ አከባቢያቸው እየተመለሱ እንዳልኾነ፤ ይልቁንም ተጨማሪ ተፈናቃዮች ወደ መጠለያው እየገቡ መሆኑን የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳዳሪው ስቡህ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
ስቡህ፤ በሁለቱ ወረዳዎች 67 ሺህ ተፈናቃዮች የነበሩ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ወቅት 4 ሺህ ተፈናቃዮች ተጨምሮ 71 ሺህ ደርሷል ብለዋል። ተፈናቃዮቹ ለከፋ ርሃብና በሽታ እየተጋለጡ መኾኑንም አስታውቀዋል።
በአበርገሌና ጻግብጂ ወረዳዎች በተለያየ ምክንያት ሳይፈናቀሉ በየ በረሀው ተቀታትነው ከቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በወሊድ፣ በርሃብ፣ በበሽታ እና በሌሎች ልዩ ልዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች የሚሰቃዩትን በርታቶች መኖራቸው የብሄረሰቡ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው አክለው እንደገለጹት ሀገራዊ ስምምነቱን የጦርነቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆነው የዋግ ህዝብ በደስታ የተቀበለው ቢሆንም አሁን ካለው የዋግ ህዝብ ችግር አንፃር ስምምነቱ በተጠበቀው ልክ ሁኖ ባለመገኘቱ ችግራችንን ማየት ያልቻለ ስምምነት ሁኖ አግኝተነዋል ብለዋል።
በጻግብጂና በአበርገሌ ወረዳዎች የህወሓት መኖሩን የገለፁት አስተዳዳሪው በዚህ ጉዳይ የክልሉንም ሆነ የፌዴራሉን መንግስት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ቡኋላም የምንፈልገው ህዝባችን እፍኝ ስንዴ እየተረዳ ስቃዩ እንዲራዘም ሳይሆን ወደ ቀየው እንዲመለስ ነው ብለዋል ስቡህ። ሀገር ሰላም ነው እየተበላና የሰላም ስምምነት በሚደረግበት በዚህ ወቅት በየቀኑ የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመኾኑ መንግስት መፍትሔ ይስጥ ሲል አሳስበዋል፡፡
በዋግ ኽምራ አስተዳደር ስር ባሉ አበርገሌ እና ፀገበጅ ውስጥ በተደጋጋሚ ትፈናቃዮች ለፍተኛ ረሃብ፣ ድርቅ እና ለከፋ ችግር ሲዳረጉ መቆየታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ስትዘግብ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ በሀምሌ ወር በተለይ አበርገሌ ወረዳ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በርካታ ተፈናቃዮች በመኖራቸው ወባ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና አጣዳፊ ትውከት በሽታ በመከሰቱ ለስምንት ሰዎች ሞት ምክኒያት መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ቢሮ ማስታወቁ የሚታወስ ጉዳይ ነው።አስ