ዜና፡ በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ለማካለልና ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለፀ
ምስል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

በብሩክ አለሙ @birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን የማካለሉ ስራ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በስምምነቱም መሰረት የፊንፊኔ ዙሪያ ውስጥ በመግባት በርቀት በአዲስ አበባ የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች ለአብነት ኮየፈጬ፤ ቱሉዲምቱ በከፊልና ጀሞ ቁጥር ሁለት የሚገኙበትን ወደ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲካለሉና የፊንፊኔ ዙሪያ የገነባውን የቆጣሪ ኮንዶሚኒየም ወይም ለቡ አካባቢ ከፉሪ ሃናና የፊንፊኔ ዙሪያ ኮንዶሚኒየሞች ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያለውን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ በማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ሁሉም ባለበት ቦታ እንዲያስተዳድር ታሪካዊ ስምምነት ላይ መደረሱንም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ላይ በሁለቱ ወገኖች  ስምምነት ላይ የተደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በተካሄደው የውይይት መድረክ ነው። ከአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተወጣጡ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች፤ አባገዳዎች፤ የሃይማኖት አባቶች፤ አገር ሽማግሌዎችና የነዋሪዎች ተወካዮች የመድረኩ ዋና ተሳታፊዎች ናቸው። የመድረኩ ዋና አላማ የተደረሰው ስምምነት የህዝቦችን አንድነትና አብሮ ማደግን በሚያጠናክርና ዘለቂ መፍትሄ በሚሰጥ መልኩ እንዲተገበር ለማድረግ መሆኑ ተነግሯል ።

የአስተዳደር ወሰን አጥር አይደለም ያሉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በህዝቦች መሃከል አጥር ልናበጅ አንችልም ብለዋል፡፡ አክለውም የአስተዳደር ወሰኑ በሚነካባቸው አካባቢዎች የትኛውም አይነት መንግስታዊ አገልግሎት አንደማይቋረጥ፣ የአገልግሎትና የፀጥታ ስራዎች በሁለቱም ወገን በጋራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰሩ፣ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች እንደማይቆሙ፤ ይልቁንም በፍጥነት የሚጠናቀቁበት ሁኔታ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ከንቲባዋ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱና የተማሪዎች የቋንቋ ጉዳይ በነበረበት እንደሚቀጥልና የሚሰጡ መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ቋነቋ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳያሳርፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የአስተዳዳር ወስን መካለል የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር፣ ዘላቂ የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን በተለይ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ወሳኝ የሆኑ የልማት ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም የመሬት ወረራን ጨምሮ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር  መፍትሄ እንደሚሆን ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሱት፡፡

ከተማ አስተዳደሩና ልዩ ዞኑ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው በጋራ እንዳያድጉና እንዳይለሙ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱም ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር ወሰን ጉዳይን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከከተማ አስተዳደሩና ከልዩ ዞኑ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥልቅ ጥናት ማካሄዱና አሁን ስምምነት ላይ መደረሱ በይፋ ተነግሯል፡፡  

ይህ የወሰን ማካለል ሂደት ተግባራዊ ሲደረግም የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት፣ የኦሮሚያ ክልል ህገ-መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር እንደመነሻ ተወስዷል ነው የተባለው፡፡ የአስተዳዳር ወሰኑ በህዝቦች ስምምነት መሰረት ማካለል ደግሞ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደርና ወሰን ጥያቄ የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት ለማጎልበት በማሰብ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ይህ ውሳኔ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ በሁለቱም አካባቢ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት እንደቀደመው ሁሉ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ መልኩም የአካባቢዎቹን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ባሉበት የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ግልፅ የሆነ የአስተዳደር ወሰን ሳይካለል በመቆየቱ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልትና በደል ሲደርስበት ቆይቷል ሲል የገለፀው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ የልዩ ዞኑም ሆነ የአዲስ አባባ ነዋሪዎች የሚገባቸውን የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም ሲል ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ አፍንጫ ስር ሆነዉ የልዩ ዞኑ ነዋሪ ልጆች የአንደኛና ሁለተኛ ትምህርት ቤትን ለመፈለግ 40 እና 50 ኪሎሜትር ርቆ ለመሄድ ተገዷል ያለው ኮሙኒኬሽኑ የአስተዳድር ወሰኑ ሲካለል የከተማ አስተዳደሩንና የልዩ ዞኑን ህዝቦች በጋራ አብሮ መልማትን፣ መሰረት ያደረገ፤ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር እንዲያጠናክር ታሳቢ ያደረገ፣ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩ ወቅታዊ ሳይሆን ዘላቂና የረጅም ጊዜ መፍትሄ እንዲሆንና ለዘመናት ይደርስ የነበረውን በደልና ጉዳት በሚያስወግድ መልኩ ተጠናቋል ብሏል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር ወሰኑ መሬት ላይ ወርዶ በሁለቱም በኩል መደበኛ ስራ እስኪጀመር ቀድሞ የነበረዉ መደበኛ የአገልግሎት አሰጣጡና የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ሳይስተጓጓሉ እንደሚቀጥሉም አክሏል፡፡

የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችና የመሰረተ ልማቶች በተያዘዉ መንገድ የሚቀጥሉ መሆኑን የጠቀሰው የመንግስት ኮሙኒኬሽኑ ዉሳኔዉ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል፣ የሕግ የበላይነትን በጋራ ለማስፈን እንዲሁም ለጋራ ልማትና እድገት ዘላቂ መፍትሔ በመሆኑ ሁሉም አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲተባበሩ ጥሪዉን አቅርቧል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.