ዜና፡ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በረዶ ቀላቅሎ በጣለዉ ዝናብ በሰብል ላይ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ማድረሱ ተገለፀ

በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በዝናብ የወደመ ሰብል ፤ መስል- ሰሜን አቸፈር ወረዳ ኮሙኑኬሽን

አዲስ አበባ፣መስከረም 20/ 2015 ዓ.ም፡- በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ከ2መቶ ሄክታር መሬት በላይ ሰብል ላይ በረዶ ቀላቅሎ በጣለዉ ዝናብ በሰብል ላይ በግምት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ማድረሱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉስ አለነ እንዳሉት ሻምብላ አብና ቀበሌ ጨሊያ ጎጥ መስከረም 8/2015 ዓ.ም በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በቆሎ በጤፍ፣ በዳጉሳ፣ በገብስ ፣አተር ፣ባቄላ ፣በርበሬ በተሸፈነው 2መቶ 37 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ሰብል ልማት ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት አድርሷል፡፡

አንድ መቶ ሃምሳ አንድ አርሶ አደሮች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል ያሉት ኃላፊው ጉዳት የደረሰባቸው ሰብሎች በምርት ዘመኑ 15ሺህ 1 መቶ 2 ነጥብ 5 ኩንታል ይገኛል ተብሎ ይጠበቅ ነበር ብሏል፡፡ ሰብሎችም በገንዘብ ሲገመቱ 16 ሚሊዮን 86 ሺህ 1መቶ 12 ብር መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በረዶው 2 ሚዮሊን 3መቶ 40 ሺህ ብር የሚገመት የ46 የአርሶ አደሮች ቤቶች እና 1 የእምነት ተቋም ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ኃላፊው ጉዳቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓቶች እና ሌሎችን የማቅረብ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ማህበረሰቡ የእርስ በርዕስ መረዳዳት ባህልን በማዳበር ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸው አቅርበዋል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ገነት ፈቃዱ እንዳሉት በዘሩት ሰብል ላይ በርዶ ቀላቅሎ በዘነበው ዝናብ ሁሉም ሰብሎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡ የነበረውን ሰብል ባይተካልኝም በቀሪ እርጥበት እንድዘራው የሚመለከተው አካል በወቅቱ ግብዓት ቢያመቻችልኝ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ሌላው አርሶ አደር ታደለ ጠብቅ እንዳሉት በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ አምስት ሄክተር መሬት ሰብላቸውን ፣ቤታቸውን እና የእንስሳት መኖአቸው የጉዳቱ ሰለባ መሆኑን ገልፀው ጉዳቱ የደረሰባቸው አርሶ አደሮች ለርሀብና ለበሽታ እንዳይጋለጡ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በወረሃ ሐምሌ በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ወረዳ በልጓማ ከተማና ዙሪያው በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ በረዶ ቀላቅሎ  በጣለው ከባድ ዝናብ በቤት እንስሳት፣ በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ ተክሎችና ቋሚ አትክልቶች፣ የስንዴና የባቄላ ሰብል እንዲሁም ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን  032 ጉምሮ ቀበሌ ከ600 ሄክታር በላይ የስንዴና የባቄላ ሰብል ሙሉ በሙሉ ማድረሱን የደቡብ ወሎ ኮሙኒኬሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.