ዜና፡ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን በአወዳይ እና ጎንደር ከተሞች ማስጀመሩን አስታወቀ

ፎቶ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2015 ዓ.ም፡- ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ያለውን የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራው በአወዳይ እና ጎንደር ከተሞች ማስጀመሩ አስታወቀ

የጎንደር እና አወዳይ ደንበኞች የሲም ካርድ ሽያጭ ምዝገባ፣ የአየር ሰዓት እና የስልክ ቀፎዎች ግዢ እንዲሁም የደንበኞች ድጋፍ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች ማግኘት እንደሚችም አክሎ ገልጿል።

በአወዳይ አንድ በቀበሌ ዐ1 የሚገኝ የሳፋሪኮም መለያ የተለጠፈበት መደብር እና በጎንደር አራት (በፒያሳ፣ አራዳ፣ አዘዞ እና ኮሌጅ) የሳፋሪኮም መለያ የተለጠፈባቸው መደብሮች ደንበኞችን ለማገልገል ክፍት ናቸው ብሏል፡፡

ይህ የአወዳይ እና ጎንደር ከተሞች የደንበኞች ሙከራ ምዕራፍ ከመንግሥት፣ ከንግድ ድርጅቶች፣ ከየአካባቢው ማህበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ድረስ በ25 ከተሞች አገልግሎቶቻችንን ለማስጀመር የሚደረገው ሒደት አካል መሆኑን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሱሳ ገልፀዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እያካሄደ የሚገኘውን የሙከራ ኔትዎርክ አገልግሎቱን እያስፋፋ ሲሆን ይህ የደንበኞች ሙከራ የሳፋሪኮምን ኔትወርክ እየሞከሩ ያሉትን ከተሞች ቁጥር 10 ማድረሱን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

በተጨማሪም የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የሚረዳ ‘700’ አጭር ቁጥር የደንበኞች አገልግሎት የጥሪ መስመር ድርጅቱ ያቀረበ ሲሆን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ድጋፍ ማግኘት እንደሚቻልም ድርጅቱ አስታውቋል።

ሳፋሪ ኮም ከዚህ በፊት በድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሐረማያ፣ ባሕር ዳር፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ እና ደብረ ብርሃን ላይ ሙከራ መጀመሩ ይታወቃል።

ድርጅቱ ከዚህ በፊት የቴሌኮም አገልግሎቱን ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመስጠት እቅድ የነበረው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተግባር አለመግባቱን ማስታውቁ ይታወሳል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተጀመረው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ኪራይ ዋጋ ላይ ከስምምነት አለመድረስ፣ የኔትወርክ ዝርጋታ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሥራ በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ እና ሌሎች ምክንያቶች ተቋሙ ባሰበው ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር እንቅፋት እንደሆነበት ጭምር ገልጦ እንደነበር ይታወሳል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.