ዜና፡ በትግራይ 30 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤ ከ5 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይሻሉ፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት

የጤና ባለሙያ መንግስቱ አታላይ የተወለደን ህፃን ሲከታተል፤ ማይ ፀብሪ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፡ ፎቶ ዩኒሴፍ- ኢትዮጵያ/ 2021/ ደምሰው ብዙወርቅ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/ 2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትላንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ከሚገኙ ህፃናት መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸው እንደዚሁም ክልሉ እየደረሰ ያለው ሰብአዊ አቅርቦት ከሚፈለገው እጅግ ያነሰ በመሆኑ ከ5 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል ከአንድ አመት በላይ የቆየው እገዳ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና በረሃብ ምክኒያት ሞት እንዲከሰት አስተዋጽኦ አድርጓል

ዩኒሴፍ ከሰኔ ወር 2021 ጀምሮ በትግራይ ክልል የህጻናት ምግብ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አሳውቆ ነበር። “በርካታ ትንንሽ እና ጨቅላ ህጻናት ለበሽታ እና በምግብ እጥረት ሊሞቱ በሚችሉበት አደገኛ ሁኔታ መኖሩን ገልፆ  “ይህ እንዲሆን አለም ሊፈቅድለት አይችልም” በማለት አስጠንቅቋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በቅርቡ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚላክ ሰብዓዊ  እርታዳ መሻሻሎች ቢታዩም የተደረገው ድጋፍ ግን ከሚያስፈልገው ያነሰ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል። አክሎም ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ብሏል።

“ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአብዛኛው የአማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች የእርዳታው ተደራሽነት ተሻሽሏል። ነገር ግን የተቸገሩትን ሁሉ ለመርዳት ስራችንን ማሳደግ አለብን” ብሏል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ።

እ.አ.አ ከህዳር 15 ቀን እስከ ህዳር 24 ቀን 2022 ዓ.ም እርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ ከ450 በላይ የጭነት መኪናዎች በመንግስት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትግራይ ገብተዋል። “ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የምግብ ዕርዳታ ሲሆን የተወሰኑት የህክምና እና የግብርና አቅርቦቶች ሲሆኑ የተወሰነ ነዳጅ እና የገንዘብ አቅርቦትን ያካትታል” ብሏል። አስፈላጊውን ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ለተቸገሩት ሁሉ እንዲደርስ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።

የትግራይ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ ለድምፂ ወያነ እንደተናገሩት ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የትግራይ ህዝብ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልገዋል። የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ እስካሁን ከ36,000 ኩንታል በላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ቢደርስም በክልሉ ካለው ሰብዓዊ ቀውስ አንፃር ሲታይ ውስን መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጀቱ  አያይዞም በኦሮሚያ በባሌ ዞን እና በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን እየተከሰተ ያለውን የኮሌራ ወረርሽኝ በመግለጽ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች መያዛቸውንና 20 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሥጋት መዳረጋቸውን ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አጋሮቹ የጤና እና የውሃ እንዲሁም የንፅህና አጠባበቅ ዕርዳታ እየሰጡ ነው ብሏል።

ግጭት በተከሰተባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሰዎች  ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ በመሆኑ  የሚደረገው ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደተገደበ መቆየቱንም ገልጿል።

በተሻሻለው የሰብአዊ እርዳታ እቅድ መሰረት እ.አ.አ. ከሰኔ እስከ ሀምሌ 2022 ዓ.ም  ድረስ የጸጥታ ችግር፣ ግጭቶችና ብጥብጥ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎትን መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 3.085 ቢሊዮን ዶላር ወደ 3.335 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል አድርጓታል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.