ዜና፡ በሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ላይ ቦንብ በመጣል የአንድ ካህን ሞትና በ16 ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሠው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

ረ/ኢንስፔክተር ክንዱ ወረቅነህ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/2015 ዓ.ም ፡- በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ በመካነ ሰላም ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ላይ ቦንብ በመጣል የአንድ ካህን ሞትና በ16 ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሠው ተጠርጣሪ በቁጥጥር መዋሉን የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ጥቃቱ የደረሠው ህዳር 16/2015 ዓ.ም ከቀኑ 9፡30 አካባቢ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ከቅዳሴ በኋላ በሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው ፀበል ጻድቅ በመቅመስ ባሉበት ወቅት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ታክቲክ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረ/ኢንስፔክተር ክንዱ ወረቅነህ ገልፀዋል፡፡ በተፈፀመው ጥቃትም አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን ህይወታቸው ሲሆን በ16 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት 16 ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና በአሁኑ ሰዓት ህይወታቸውን ለማትረፍ የህክምና ባለሙያዎቹ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እነደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃ/ማርያም ታረቀ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

ረ/ኢንስፔክተሩ የደቡብ ወሎ የዞን መርማሪ ቡድን ከቦረና ወረዳና መካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የፀጥታ መዋቅር ጋር በተደረገ የተቀናጀ ምርመራ ተጠርጣሪው በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን  ገልፀዋል፡፡

ረ/ኢንስፔክተሩ አያይዘው እንደተናገሩት በደረሰው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ እና ምርመራ መቀጠሉን ገልፀው ድርጊቱን ከተለያየ አቅጣጫ በማያያዝ ህብረተሰብን ለማጋጨት የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንዲሁም ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጎን በመቆም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅና ለፀጥታ መዋቅሩ ተባባሪ እንድሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.