ዜና፡ በትግራይ የምግብ እርዳታ ስርቆቱ እየተጣራ ባለበት ወቅት በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፤ የቀጠለው የሰብዓዊ እርዳታ መቋረጥ ለችግሩ ሰበብ ሆኗል

በምህረት ገ/ክርስቶስ @MercyG_kirstos

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23/2015 .ም፡ በትግራይ ክልል ሲደረግ የቆየው ሰብዓዊ ርዳታ እንዲቋረጥ ምክንያት የሆነውን የምግብ ዕርዳታ ስርቆት ለማጣራት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ወቅት በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሸቀበ መምጣቱን የክልሉ ኃላፊዎች ገለጹ።

የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ጊዚያዊ አስተዳደሪ አቶ ተክላይ ገ/ምድህን፤ በዞኑ ባለፉት 3 ወራት ውስጥ ከ270 በላይ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑት የሞቱት በሽረ፣አሰገድ፣እንዳባጉና እና ዳኤሮ የተፈናቃይ መጠለያ ውስጥ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በዞኑ ገጠራማ አካበቢዎች መሆናቸውን ገልፀዋል

“ነገሮች ይበልጥ እየከፉ ነው፣ ሰዎች በየቀኑ እየመቱ ነው” ያሉት ተክላይ፣ ወደ እናዳባጉና የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በምስራቅ ትግራይ ዞን 15 ሰዎች በኢሮብ እና ሃወዘን ወረዳዎች በረሃብ የሞቱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ህፃናት መሆናቸውን የዞኑ ጊዚያዊ አስተዳደር ሹሻይ መረሳ አስረድተዋል፡፡

“የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ተፈናቃዮቹ አስከፊ ሁኔታ ላይ ናቸው፣ ልጆቻቸውን ይዘው በየቦታው እየለመኑ ይገኛሉ ይህ በጣም አሳዛኝ ነው” ሲል ሹሻይ ተናግሯል።

የኢሮብ ወረዳ ወሳኝ ክፍልን ጨምሮ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች በኤርትራ ሃይሎች መያዛቸው አጠቃላይ ሰብአዊ ቀውሱን ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል ያሉት አቶ ሹሻይ የ15ቱ ሰዎች ህይወት ያለፈው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ባሉ አካባቢዎች መሆኑን ጠቁመዋል።

በምስራቅ ትግራይ ዞን፣ ወደ 250,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች እና 1.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች ፤ በሰሜን ምዕራብ ዞን ውስጥ፣ ግማሽ ሚሊዮን ተፈናቃዮች እና አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአካባቢው ሃላፊ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የሰብአዊ እርዳታዎች መቋረጡ በይፋ ቢገለጽም፣ ኃላፊዎቹ ግን የምግብ ርዳታ ስርጭቱ የተቋረጠው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ በፊት መሆኑን ይናገራሉ።

“ሰብዓዊ እርዳታው ከቆመ አምስት ወር ሆኗል፤ ከመቋረጡ በፊትም በቂ እርዳታ አልነበረንም” በማለት የትግራይ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነርና የአበዓዊ እርዳታ ስርቆቱ መርማሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ገብረህይወት ገ/ እግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡

“የሰብአዊ እርዳታ በመቋረጡ የተነሳ ረሃብና የዜጎች ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል” ያሉት ገብረህይወት፣ “ክልሉ ምርመራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ ነው” ብለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በክልሉ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ግብረ ሰናይ ድርግቶችና መንግስት የተቋረጠውን እርዳታ እንዲያስቀጥሉ እና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በዋና ዋና ከተማዎች ሰልፍ በማድረግ ጠይቀዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ የሰብአዊ ርዳታ ስርቆት ምርመራው ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ እንዲጠናቀቅ እና ወንጀለኞቹ ተለይተው በህግ እንዲጠየቁ ጠይቀዋል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም ሚያዚያ 25 ባወጣው መግለጫ የተቋረጠው የምግብ ስርጭት ለተላከላቸው አካላት መድረሱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ተቋርጦ የሚቆይ መሆኑን ገልጧል፡፡ ዩኤስኤአይዲም በእለቱ ባውጣው መግለጫ “በትግራይ ክልል ድርጅቱ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ ላለልተወሰነ ጊዜ ለማቆም ከባድ ውሳኔ ማሳለፉን” አስታውቋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.