ዜና፡ በአፋር ክልል በተከሰተ የደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2015 ዓ.ም፡- በሰሜናዊ ምስራቅ የአፋር ክልል አከባቢ በተከሰተ የደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው ሳምንታዊ ሪፖርቱ አስታወቀ። እስከ ግንቦት 13 ቀን 2015 በአጠቃላይ 1638 በደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝ በሽታ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ያመላከተው ሪፖርቱ በሽታው በስፋት የተሰራጨው በሚሌ ወረዳ መሆኑን ገልጿል።

በወረርሽኙ መያዛቸው ሪፖርት ከተደረጉ የክልሉ ሰዎች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት ከሚሌ ወረዳ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። ከሚሌ በተጨማሪ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን የሎጊያ ወረዳም በወረርሽኙ ተጠቂ መሆኗን ሪፖርቱ ጠቁሟል።  

የአለም የጤና ድርጅት ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ከመጋቢት 26 ቀን 2015 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑን አስታውቋል። አብዘሃኛው በወረርሽኙ ተጠቂ የሆኑት ከአስራ አምስት አመት በላይ እድሜ ያላቸው መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ በዋናነት የታዩት ምልክቶችም የሰውነት መገጣጠሚያ ህመም፣ የራስ ምታት፣ ትውከት እና ትኩሳት መሆናቸውን ገልጿል።

ደንጊ ትኩሳት / dengue fever/ የሚባለው የበሽታ አይነት ደንጊ በሚባል ቫይረስ የሚተላለፍ ሲሆን ቫይረሱን ወደ ሰው የሚያስተላልፉት ደሞ ቫይረሱን የተሸከሙ ጥቃቅን ትንኞች ናቸው። የህመሙ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው በትንኙ ከተነደፈ ከ 3 ቀን እስከ 2 ሳምንት ባለው ጊዜ ነው። የህመሙ ምልክቶችም ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ በቆዳ ላይ የሚከሰት ሽፍታ፣ የአጥንትና የመገጣጠሚያ ህመም ተጠቃሽ ናቸው።

ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ወር የታየው የአጭር ግዜ ዝናብ ሳቢያ የአፋር ክልል በቅርቡ በጎርፍ ከተጠቁ የኢትዮጵያ ክልሎች መሆኑን የጠቆመው የአለም የጤና ድርጅት በዝናቡ ምክንያት ውሃ የቋጠሩ ኩሬዎች ለትንኞች መፈልፈያና መራቢያ መሆናቸውን አመላክቷል። የአፋር ክልል አከባቢ ከደንጊ ትኩሳት ወረርሽኝ በተጨማሪ የወባ ወረርሽኝ እንደሚያጠቃው ድርጅቱ በሪፖርቱ አካቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.