ዜና፡ ሩሲያ ሰራሽ መኪኖች በኢትዮጵያ ሊገጣጠሙ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2015 ዓ.ም፡- የሩሲያ መኪና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መገጣጠሚያ ለመመስረት እንደሚፈልጉ በአዲስ አበባ የሀገሪቱ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርከሂን ማስታወቃቸውን ሩሲያ ቱደይ ዘግቧል። በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱም ሀገራት እየተወያዩ መሆናቸውን አምባሳደሩ መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል።

በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል ያለው የቢዝነስ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው ዘገባው ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በ2022 የ18 ቢሊየን ዶላር ግብይት መካሄዱን አመላክቷል።

ኢትዮጵያ ለሩሲያ የምታቀርበው ዋነኛ ምርት ቡና መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ሩሲያ ወደ ኢትዮጵያ ካቀረበችው ምርቷ ገሚሱ ስንዴ መሆኑን እና በተጨማሪም የዘይት ውጤቶች፣ የወረቀት ምርቶች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት የሩሲያ ፓርላማ ዱማ ሊቀመንበር ከኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ጋር መገናኘታቸውን እና በሀገራቱ የኢኮኖሚ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውን ዘገባው አውስቷል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉን አጋሮች ዋነኛዋ ናት፤ መሰል ውይይቶችን በማድረግ ላለፉት 125 አመታት ግንኙነቶቻችንን አስጠብቀናል ሲሉ የዱማው ሊቀመንበር ቪያቸስላቭ ቮሎዲን መናገራቸውን ዘገባው አካቷል። በተጨማሪም የሪሲያ ኩባንያዎች በማዕድን ማውጣት፣ በሀይል አቅርቦት፣ በትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽን እና ግብርና ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ዘላቂ ግንኙነት መመስረት እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ከሩሲያ ጋር ያለን ግንኙነት ጠንካራ ቢሆንም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ይበልጥ መጠናከር ይገባዋል ማለታቸውን ሩሲያ ቱዴይ ቴሌቪዥን በዘገባው አስታውቋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.