በፍራኦል በርሲሳ
አዲስ አበባ፡ የሀዲያ እና የስልጤ ዞን ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በስልጤ ዞን በአብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ሚያዚያ 20, 2014 ቀን መግለጫ ሰጥቷል። በተመሳሳይ የክልሉ መንግስትም ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃቶችን እንደማይታገስ ትናንት ባወጫው መግለጫ አስጠንቅቋል።
የሀዲያ እና የስልጤ ዞን ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ሚያዚያ 20 ቀን “አንዳንድ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ የወጡ አክራሪዎች” ሰላት ከፈፀሙ በኋላ መፈክሮችን በማሰማት ወደ ወራቤ ከተማ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ-ክርስቲያን በመሄድ ጉልላቱን በማውረድ ከዛም ንዋያተ ቅድሳቱን ወደ ወጪ አውጥቶ በማቃጠልና ከቃጠሎ የተረፈውን ቤተ ክርስቲያንም በማፈራረስ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም እንዳይሰጥ ማድረጋቸው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በደብዳቤው ላይ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮችና የጥበቃ ሠራተኞች ላይ ድብደባ በመፈጸም እና በከተማው የሚገኙ የክርስቲያን ሆቴሎች ላይም ጉዳት አድርሰዋል ሲል አብራርቷል ። ይህም በስልጤ ዞን የሀይማኖች መካከል ላለው መስተጋብር አሉታዊ ተፅእኖ ከማድረጉም በላይ በአጎራባች አካባቢዎች ችግሩ እንዲስፋፋ አድርጓል።
ሁከቱ እየሰፋ በመሄድ በሳንኩራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ በሙሉ ውድመት መድረሱን የገለጸው ደብዳቤው፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት “ የዞን የጸጥታ ኃይል ጣልቃ በመግባት ሁከቱን ማስቆም ባለመቻሉ እጅግ እንዳሳዘነውም ገልጿል። ሀገረ ስብከቱ እነዚህን የሁከት ድርጊቶች በጽኑ አወግዟል።
በመጨረሻም መግለጫው የፌደራልና የክልል መንግስታት በአደጋው የተጎዱ አገልጋዮችና ክርስቲያኖች ሕክምና እንዲያገኙ፣ የስልጤ ዞንና ወረዳዎች የሚገኙ ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት አስቸኳይ እርዳታና ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና ተግባሩን የፈጸሙ ወንጀለኞች ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርቡና ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲሰጣቸው ጥሪ እቅርቧል ።
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል መንግስት ትናንት በሰጠው መግለጫ የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን እየሰሩ ያሉትን በሀገራዊ ለውጡ ያልተደሰቱና የግል ጥቅማቸው ተነካብን ብለው የሚያስቡ ቡድኖችን ወቅሰዋል። አክሎም ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት እንደማይታገስም ነው ያስታወቀው።
የህግ ማስከበር ስራ ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው መግለጫው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ሀይማኖትን ሽፋን አድርጎ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ለማንም እንደማይጠቅሙ ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስቧል። ‘ህዝቡ መሰል ድርጊቶችን የማውገዝ ብቻ ሳይሆን የመከላከል ሃላፊነትም አለበት’ ሲል አክሏል።
መግለጫው “አክራሪ ሃይሎች” ያላቸውን በስም ባይጠቅስም “በብሔር ተኮር አክራሪነት” የተጠመዱ መሆናቸውን በመግለጽ “ዘመቻውን የሃይማኖት መልክ ለማስያዝም እያስፈፉ ነው” ብሏል።
የክልሉ መንግስት በወራቤ ከተማ የተፈፀመውን ጥቃት ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ለረጅም ጊዜ በቆየው የሀይማኖት አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብሏል።የክልሉ መንግስት በሃይማኖት ተቋማትና ንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃቱን የፈጸሙ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርብ ገልፆ ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ ድርጊቱ እንዲፈጸም ስምሪት የሰጡ አካላት ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አክሎ አስታውቋል።
የክልሉ ወጣቶች “የክፉ ተግባር እና የጸረ ሰላም ሃይሎች” መሳሪያ ከመሆን እንዲቆጠብና የህዝቦችን አንድነት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል። የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች በፀረ-ሰላም አካላት የሚደረጉ ደባዎችን በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ እንዲጠብቁ አሳስቧል። አስ