በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚገኙ የቱርክ ዜጎች እሁድ እለት ከአገሪቱ የሚወጡበትን ቀን ሲጠባበቁ። ፎቶ፡ Omer Erdem/Anadolu Agency
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16/2015 ዓ.ም፡- ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ቀናት በርካታ ሀገራት በሱዳን የሚገኙ ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ሲጣደፉ ተስተውሏል። ሀገራቱ ዜጎቻቸውን ለማስወጣት በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያን ትብብር እያገኙ እንደሚገኙ የየሀገራቱ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። የአሜሪካ መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ዜጎቹን ከሱዳን ማስወጣቱን አስታውቆ ለዚህ ተግባሩም ኢትዮጵያን ጨምሮ ጅቡቲ እና ሳዑዲ አረብያን አመስግኗል።
የኬንያ መንግስት አንድ መቶ የሚሆኑ በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ዜጎቹን በኢትዮጵያ በኩል ማስወጣቱን የሀገሪቱ ጋዜጦች አስነብበዋል። ኬንያውያኑ በጎንደር በኩል መውጣታቸውን ያስታወቁት ዘገባዎቹ በኬንያ የነጻነት ታሪክ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን የመታደግ ስራ ተሰርቷል ሲሉ አወድሰዋል።
በሌላ በኩል በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ናይጀሪያውያን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጅቶቻቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ። በናይጀሪያ ተማሪዎች ብሔራዊ ማህበር ባስተላለፈው መልእክት እንዳስታወቀው በሱዳን የሚገኙ ተማሪዎች በገዳሪፍ ከተማ በሚገኙ በሶስት ቦታዎች ላይ እንዲሰባሰቡ አሳስቦ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው የማስወጣት ስራ ይከናወናል ብሏል። በጉዳዩ ዙሪያ የናይጀሪያ መንግስት ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ በቤታቸው እንዲቆዩ እና ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አሳስቧል። ወደ ድንበር አከባቢ መጓዝ አደገኛ መሆኑን ያስጠነቀቀቅ በሱዳን የናይጀሪያ ኤምባሲ ዜጎቹን ለማስወጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
የጃፓን ጠ/ሚኒስትር ዛሬ ማለዳ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር ዜጎቹን በሰላም ለማስወጣት እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል።
የፈረንሳይ መንግስት አንድ መቶ የሚደርሱ ዜጎቹን ከሱዳን ማስወጣቱን አስታውቋል። ከፈረንሳውያኑ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናትንም እንዲወጡ ማድረጉን አስታውቋል።
ከአንድ ሳምንት በላይ ያስቆጠረው የሱዳን ቀውስ ጎረቤተሮቿን ከማስጨነቁ ባለፈ ሀያላን ሀገራትን እንዳሳባቸው መዘገባችን ይታወሳል። ሮይተርስ የዜና ወኪል ያስነበበው ትንታኔ እንደሚያመላክተው የሱዳን ጎረቤቶች እና ሃያላኑ ሀገራት በየራሳቸው ምክንያቶች ሁኔታውን በትኩረት በመከታተል ይገኛሉ። ግብጽ በናይል ውሃ ያላት ጥቅም፣ ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ጉዳይ፣ ሀያላኑ ሀገራት በቀጣይ የሚመሰረተው የሱዳን መንግስት ምን አይነት ቅርጽ ይኖረዋል፣ አሰላለፉ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ፣ የአውሮፓ ሀገራት ስደተኛ ሊመጣብን ይችላል የሚል ስጋት፣ ሌሎች ደግሞ የሚፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ እንዳስጨነቃቸው እና እንዳሳሰባቸው በዝርዝር ተቀምጧል። (መረጃዎቹን ከዋይትሃውስ፣ ከኤንኤችኬ፣ ኬንያንስ ድረገጽ፣ ከናጋላንድፖስት አገኘነው)