ዜና፡ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ 88በመቶ ማደጉ ተገለጸ፤ በፈረንጆቹ 2022 አንድ ቢሊየን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተገልጿል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16/2015 ዓ.ም፡- በሲዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው አለም አቀፉ የሰላም ጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 ለሚሊተሪ አንድ ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 88በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተቋሙ አመላክቷል።

እንደ ተቋሙ መራጃ ከሆነ ጭማሪው የታየው ሀገሪቱ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ከትግራይ ሀይሎች ጋር ያደረገችው የእርስ በርስ ጦርነት ጋር የተገናኘ ነው።

በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት የነበረው ወታደራዊ ወጪ እጅግ ከፍተኛው መሆኑን ያመላከተው ተቋሙ የሀገራት ወታደራዊ ወጪ ባሳለፍናቸው ስምንት አመታት በተከታታይ የሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል። ከአለማችን ሀገራት መካከል ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ያከናወኑ ሶስቱ ሀገራት አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መሆናቸውን የጠቆመው ተቋሙ የሶስቱ ሀገራት ወጪ የአጠቃላይ የአለም ሀገራትን 56 በመቶ እንደሚሸፍኑም ገልጿል።

ተቋሙ በጥናት እንደለየው ከሆነ ባሳለፍናቸው ስምንት አመታት በከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ወጪያቸው የጨመረው የአውሮፓ ሀገራት ሲሆኑ የ13 በመቶ ጭማሪ ማድረጋቸውን አመላክቷል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በአለም አቀፍ ደረጃ ወታደራዊ ወጪ እያደገ መምጣቱ በአለም ላይ አለመረጋጋት መስፈኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ የተናገሩት የተቋሙ ከፍተኛ አጥኚ ናን ትያን እየላሸቀ የመጣውን የጸጥታ ማጣት ስሜት መሻሻል አያሳይም በሚል ሀገራት ወታደራዊ አቅማቸውን እያፈረጠሙ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.