ዜና፡ በህገወጥ መንገድ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ 58,833 የዉጭ ሀገራት ዜጎች መመዝገባቸው ተገለጸ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- በህገወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ህጋዊ የማድረግ ምዝገባ ሂደት እስከ ሐምሌ 20/ 2014 ዓ.ም ድረስ ሀምሳ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ ሠላሳ ሦስት( 58,833 ) የሚሆኑ የዉጭ ሀገራት ዜጎች መመዝገባቸውን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ

ቢሮው እንዳስታወቀው ተመዝጋቢዎቹ ከካናዳ፣ አሜሪካ፣ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ቡርንዲ፣ ጋና፣ ባንግላዲሽ፣ ሕንድ፣ ላይቤሪያ፣ ካሜሮን፣ ጣሊያን የመጡ ሲሆኑ ህገ ወጥ የዉጭ ሀገር ዜጎችን ህጋዊ ለማድረግ በተጀመረዉ ምዝገባ ሂደት በተናጠል የአንድን ሀገር ዜጋ ላይ ሊተገበር የተላለፈ ውሳኔ አለመሆኑን ገልጿል።

መስሪያ ቤቱ መመዝገብ የሚቻልበትን  ቅድመ ሁኔታ ያስታወቀ ሲሆን ምዝገባው የሚመለከታቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መንገድ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር ዜጎች ሆነው ጊዜው ያለፈበት ቪዛ ያላቸው፣ ጊዜው ያለፈበት የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው፣ የኢሚግሬሽን ስርዓት ሳይፈጽሙ ምንም አይነት የቪዛም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው፣ የከተማ ስደተኞች ሆነው የስደተኝነት መታወቂያ ያላቸውና የስደተኝነት ጥያቄ አቅርበው በሂደት ላይ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ሲል ዘርዝሯል።

ህጋዊ ሰነድ ማለትም ጊዜው ያላለፈበት ቪዛና ጊዜው ያላለፈበት የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የሚንቀሳቀሱና የሚኖሩ ማንኛንም የውጭ ሀገር ዜጎችና የተመዘገቡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጊዜው ያለፈበትም ሆነ ያላለፈበት መኖሪያ ፈቃድና ቪዛ ያላቸው የውጭ ዜጎች  ምዝገባው የማይመለከታቸው ናቸው ሲል አክሎ ገልጿል።

ምዝገባው ሁለት ምዕራፍ ያለው ሲሆን የመጀመሪያ ምዕራፍ እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ/ም የሚቆይና በርከት ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚንቀሳቀሱትና የሚኖሩት አዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የሚከናወን ሲሆን በምዕራፍ ሁለት ደግሞ ሁሉም የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሪቷ ውሰጥ በሚገኙ ክልሎች በሙሉ ድሬደዋ መስተዳደርን ጨምሮ የሚከናወን ይሆናል፡፡ በምዝገባው የጊዜ ገደብ ውስጥ በወቅቱ ለማይመዘገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች የአገልግሎት መ/ቤቱ ህጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን አሳውቋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የመመዝገቢያ ጣቢያዎችንም ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት በኢዲስ አበባ ባሉ 121 የመመዝገቢያ ጣቢያዎች እና ፒያሳ የሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት እንዲሁም  በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ደግሞ፡- ገላን፣ ዱከም፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ እና ሰበታ እንዲሁም ቢሾፍቱ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፅ/ቤቶች ምዝገባ በመከናወን ላይ ይገኛል ብሏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.