በአሰፋ ሞላ @AssefaMolla6
አዲስ አበባ፣መስከረም 25/2015 ዓ.ም፡- ከስልሳ አመታት በላይ ከሀገሪቱ ተወስድው የነበሩ 11 የብራና ቅርሶች ሮቤን ሃውስ በተባሉ እንስት ተሰብስበዉ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት ኤጀንሲ ጥንታዊ ስነ-ፅሁፍ ማደራጃ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግዛው ዋቅጅራ ለአዲስ ስታንድርድ ገለፁ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 19 በአዲስ አበባ በተካሄደው በ21ኛው አለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ ሮቢን ሃውስ ለስልሳ አመታት ከኢትዮጵያ ውጪ የነበሩ 11 የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎችን (የብራና ላይ ጽሑፎች) ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርጋለች።
በኢትዮጵያ ታሪካዊ የብራና ፅሑፎች የተሳብችው ነዋሪነቷ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሆነው ሮቤን ሃዉስ ጠፍተው የነበሩ ቅርሶችን በግዥ መልክ አሰባስበው ለብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሕፍት ኤጀንሲ ገቢ አድርጋልች፡፡
ሮቤን እነዚህን ከሃገሪቱ ጠፍተዉ የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች በግዥ ለማሰባሰብ ስድሰት ዓመታትን ፈጀባቸው ሲሆን፣ ከተሰበሰቡት 11 የብራና ቅርሶች ውስጥ ሁለት መፅሐፈ ቅዳሴ፣ ማህሌተ ፅጌ፣ ድርሳነ ያዕቆብ፣ ድርሳነ ሚካኤል እና ስድስት የመዝሙረ ዳዊት መፅሃፍት መሆናቸዉን ለአዲስ ስታንዳርድ የተላክ ማስረጃ ያስረዳል፡፡
ቅርሶቹ በወቅቱ በግብርና ስራ ተሰማርተው በነበሩ ጀርመናዊ ቤተሰቦች 1950 እስከ 1952 ዓ.ም ከግለሰቦችና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ በተለያዩ ቁሶች እና የህትመት ውጤቶች እየተለወጡ ተሰብስበው የተወሰዱ መሆናቸዉ ተገልፀዋል::
ሮቤን ሃውስ በአትዮጰያ የብራና ቀርሶች ላይ ምርምር በማድረግ በሚታወቁት በፕሮፌሰር ሰቴቭ ዴላማረተር እገዛ የሃገሪቱ ታሪካዊ ቅርሶች በመሆናቸው ለጥናትና ምርምር ሊገለግሉ ይችላሉ በሚል እሳቤ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
ታሪካዊ የብራና ቅርሶቹን ለመጠበቅ እና ለጥናትና ምርምር ይረዳ ዘንድ ዲጂታላይዝ መድረጉ አስፈላጊ በመሆኑ፣ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከመስከረም 7 እስከ መስከረም 12፣ 2015 ዓ.ም ወደ ዲጅታል መረጃ የተቀየሩ መሆናችውም በቀረበው ፅሁፍ ላይ ተመልክተናል፡፡
የጥንታዊ ስነ-ፅሑፍ ማደራጃ ባለሙያዉ አያይዘውም ፕሮፌሰር ሰቴቭ ዴላማርተር ከ4800 በላይ የብራና እና የአረብኛ ጽሑፎችን ዲጅታላይዝ አድርገው ለብሔራዊ ቤተመፅሐፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ገቢ መድረጋቸውን የኤጀንሲዉ ጥንታዊ ስነ-ፅሁፍ ማደራጃ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግዛው ዋቅጅራ አክለው ገልፀዋል፡፡አስ