ዜና፡ የትግራይ ክልል መንግስት በአፍሪካ ህብረት የቀረበለትን የድርድር ግብዣ መቀበሉን ገለፆ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠየቀ

የትግራይ ክልል ፕረዜደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ፒኤችዲ)፤ ምስል- ትግራይ ሚዲያ ሀውስ

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖርተሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26/2015 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል መንግስት ትላንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ በአፍሪካ ህብረት የቀረበለትን የሰላም ድርድር ግብዣ እንደተቀበለ ገልፆ፣ ነገር ግን በሰላም ውይይቱ ተጨማሪ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች ወይም ዋስትና ሰጪዎች የሚጋበዙ እንደሆነ፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አይነት ሚናዎችን ሊሰጥ እንደታሰበ እና ለተደራዳሪ ቡድኑ የሎጅስቲክስ፣ የጉዞ እና የደህንነት ዝግጅቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

“የድርድር ቡድናችንን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጁ ነን፡፡ ሆኖም ስለግብዣው ቀደም ብሎ ያልተማከርንበት መሆናችንን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ለድርድሩ አመርቂ ጅምር፣ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማለትም ተሳታፊዎች፣ታዛቢዎች ወይም ዋስትና ሰጪዎች የሚጋበዙ እንደሆነ” ማብራሪያ ቢሰጠን” ሲሉ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል(ፒኤችዲ) በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የተላከው ደብዳቤ “ግጭቱን ማቆም የዋና አጀንዳችሁ አካል መሆኑን ማወቅ ለሰላም ሂደቱ ጠቃሚ ይሀናል” በማለት ደብዳቤው ገልጿል፡፡

የትግራይ ክልል ይህን መግለጫ ያወጣው መስከረም 21 ቀን በአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ተፅፎ ለፕሬዝዳንት ደብረፂዮን ከእሁድ መስከረም 29 ቀን ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ በታቀደው “የሰላም ድርድር” ላይ እንዲገኙ የተላከውን የግብዣ ደብዳቤን ተከትሎ ነው።

የአፍሪካ ህብረት ደብዳቤው “በሁለቱ ወገኖች ማለትም በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚካሄደው የሰላም ስምምነት የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው ድርድር እንዲኖር መሰረት ለመጣል በተዘጋጀው መሪ መርሆዎች፣ አጀንዳዎች እና የጊዜ ሰሌዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል” ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ለ21 ወራት የዘለቀውን ጦርነት እልባት ለመስጠት የአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን የሰላም ድርድር ግብዣ መቀበሉን የፌዴራል መንግስት ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመግለጫው “የአፍሪካ ህብረት ይፋዊ ግብዣ ከኢትዮጵያ መንግስት ቀደምት አቋም ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ደርድሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲደረግ የኢትዮጵያ መንግስት መግለፁ ይታወሳል” ብሏል፡፡

የፌዴራሉ መንግስት ቀደም ሲል “በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድሩ መጀመር አለበት” ብሎ መናገሩ ይታወሳል፡፡

የትግራይ መንግስት መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በጠንካራ የሰላም ድርድር ሂደት ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅቻለሁ” ማለቱ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም የትግራይ መንግስት ለድርድር ዝግጁ መሆኑንና ግጭቱን በማቆም የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ የትግራይ ክልል ፕሬዝዴንት አማካሪ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን እና የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም የነበሩትን ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን የድርድሩ አካል አድርጎ የሰየመ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይህ የሰላም ድርድር ሙከራ ሁለቱ አካላት ጦርነቱን ለማቆም ለአምስት ወራት የቆየውን ድርድር በመስበር ጦርነቱን ነሃሴ 24 2014 . እንደገና ከጀመሩ በኋላ የመጀመሪያው ነው

በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የተፃፈው ደብዳቤ እንደሚገልፀው ድረድሩ በአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ተወካይና የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዴንት ኦሊሰጉን ኦባሳነጆ መሪነት እና በታዋቂ አፍሪካውያን ቡድን ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል፡፡ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዴንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋምዚሌ ሚላምቦ ንጉካ ለሰላም ድርድር ሂደቱ ተሳታፊዎቸ ሆነው ይገኛሉ፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.