አቶ ካሳሁን ፎሎ-የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት፤ ፎቶ- ከክምችት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21/ 2015 ዓ.ም፡- መንግሥት ሠራተኞች በሚጠቀሙበት አነስተኛ የሻይ ቤቶች ጭምር የሚከፈለው የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሣ እንዲሁም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ደንብን ተግባራዊ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጠየቀ፡፡
ኢሰማኮ ይህንን የጠየቀው ሰኞ ሚያዚያ 23 የሚከበረውን የ2015 ሜይ ዴይ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሲሆን የዘንድሮው ሜይዴይ በዓል “ለሠራተኞች መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሄ” በሚል መሪ ቃል “በሰላማዊ ሰልፍ” እንደሚከበርም አስታውቋል፡፡
ለሠራተኞች የሚከፈለዉ እጅግ አነስተኛ የሆነዉ ደመወዝ ተመጣጠኝ አለመሆኑን የገለፀው ኢሰማኮ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል (Minimum Wage) በሀገራችን ተግባራዊ እንዲሆን፤ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ደንቡን እንዲያፀድቅ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኞች በሚጠቀሙበት አነስተኛ የምግብና የሻይ ቤቶች ጭምር የሚከፈለው የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሣ አጥብቆ ጠይቋል፡፡
ሠራተኞች በህግ ያገኙት መብት ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ ቀጥሏል ያለው መግለጫው ሠራተኛ ዛሬ ራሱንና ቤተሰቡን ማኖር ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሞ እየጨመረ በመጣው የዓለም የነዳጅ ዋጋ ምክንያት የትራስፖርት ክፍያ፣ የእህልና የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ኪራይ በእጥፍ ከመጨመሩም በላይ፤ በሀገራችን በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነትና ድርቅ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን እያባበሰዉ ይገኛል ብሏል፡፡
ከረጅም ዓመታት በፊት በወር ብር 600 እና ከዚያ በታች ደመወዝ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞች ከሥራ ግብር ነፃ የተደረጉበት ሁኔታ፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ወቅታዊ የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ ስለነበር፤ አሁን ግን ከግብር ነፃ የተደረገዉ የብር መጠን ካለው የዋጋ ንረት ጋር ስለማይመጣጠን፤ ከግብር ነፃ የሚደረገው አነስተኛ ወርሃዊ የደመወዝ መጠን ወደላይ ከፍ መደረግ አለበት ብሏል፡፡ በተጨማሪም የብር 10,800.00ና ከዚያ በላይ ተከፋዮች የ35% የሥራ ግብር እርከን መቶኛዉ ተቀንሶ መነሻውም ወደላይ ተሻሽሎ ከፍ እንዲደረግም አሰማኮ አሳስቧል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ134ኛ፤ በሀገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓሉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በአዳማ፣ በጅማ፣ በሐዋሣና በድሬዳዋ ከተሞች “በሠላማዊ ሠልፍ” የሚከበር መሆኑን ኢሰማኮ ገልፆ መንግሥትም ለሚቀርቡ የሠራተኛ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ እንዲሰጠ ጠይቋል፡፡አስ