ዜና፡ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22/ 2015 ዓ.ም፡- በህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የግድያ ዒላማ በማድረግ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር በመቆጣጠር የፌደራል መንግሥትን ለመጣል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተደራጅተው እና ተቀናጅተው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደተደረሰባቸው ግብረ- ኃይሉ ለመገኛኛ ሚዲያ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ የተባለ ግለሰብ የጽንፈኛ ኃይሎችን የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢንተለጀንስ፣ የፋይናንስ እና የሚዲያ ክንፍ እንደሚመራው የገለፀው መግለጫው 16 ጽንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ጋር ትስስር በመፍጠር በሚያገኛቸው የሎጀስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፎች በአማራ ክልል ከባህርዳር ከተማ ጀምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ታጣቂዎችን የመመልመል፣ የማሰልጠን፣ የማስታጠቅና የማሠማራት ተግባር በማከናወን በክልልና በፌደራል ደረጃ ሽብር እና ግድያ እንዲፈጽሙ ተልዕኮ ሲሰጥ እንደነበር በተደረገ ክትትል እና ምርመራ ተደርሶበታል ብሏል፡፡

ለዚህም በለጠ ሸጋው እና  ምሕረት ወዳጆ ወይም በቅጽል ስሙ ምሬ ወዳጆ በተባሉት የጽንፈኛ ኃይሉ ታጣቂ መሪዎች እና ግብረ-አባሮቻቸው ሰሞኑን በትውልድ በቀያቸው ግፍና ጭካኔ በተሞለበት አኳሃን የተገደሉት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ እና የጥቃት ሰለባ የሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ማሳያ ናቸው ብሏል የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ።

ሃይሎቹ ዓላማቸውን ለማስፈጸም በአማራና በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ 130 ወረዳዎች የመለመላቸውንና በህቡዕ ያዘጋጇቸውን 450 ግለሰቦች የአማራ ክልል ህዝብ የመረጣቸውንና በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላይ ያስቀመጣቸውን በኃይል በማስወገድ በራሳቸው መዋቅር የመተካት ሥራ ሲሰሩ እንደነበር  በክትትል እና በምርመራ የተደረሰባቸው መሆኑን አስታውቋል።በተጨማሪም ጽንፈኛ ኃይሎች የክልሉን የፀጥታ ኃይልንም በራሳቸው ታጣቂዎች ለመቀየር ተዘጋጅተው እንደነበር የተገኛው መረጃ ማመላከቱን ገልጿል።

ዶ/ር መሥፍን  ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ግሩም ላቀውና ሌሎችም በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የጽንፈኛ ኃይሉ ተባባሪዎች ከውጭ ሆነው የፖለቲካ ክንፉን እንደሚያስተባብሩ፤ አንተነህ ብርሃን፣ ወርቁ ጓዴና ሌሎችም ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ እንዲቀበሉና ለሽብር ተልዕኮ ማስፈፀሚያ እንዲያውሉ የባንክ አካውንት እንደተከፈተላቸው በክትትልና በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ፤ ቴዎድሮስ አስፋውን ጨምሮ ሌሎችም በዚሁ የሽብር እንቅስቃሴ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

በተጨማሪም በመስከርም አበራ የእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎችን የሚዲያና ፕሮፓጋንዳ ክንፍ እንደሚመራ ገልፆ በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ከሀገር ውስጥ ዳዊት በጋሻው የተባለ ግለሰብ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ደግሞ ከኢትዮ 360 እና መረጃ ቲቪ ሀብታሙ አያሌው፣ ምንአላቸው ስማቸው፣ ብሩክ ይባስ እና እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ  እንዲሁም ዘመድኩን በቀለ እና ልደቱ አያሌው ከአንከር ሚዲያ  መሳይ መኮንን እና ሌሎች ግለሰቦች የዚህ እኩይ ዓላማ አስፈፃሚ አባላት መሆናቸውን በምርመራ መረጋገጡን የግብ-ኃይሉ ምግለጫ ገልጿል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በሀሰት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም በህቡዕ አደረጃጀቱ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም  ጭምር በሽብርተኝነት ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ተገልጧል፡፡

እነዚህ የሽብር ኃይሎች ከሚኖሩባቸው ሀገራት በአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም  እነሱ ከሚኖሩባቸው ሀገራት መንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በተመሠረቱ የትብብር ማዕቀፎች አማካኝነት ወደ ሀገር ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ በህግም እንዲጠየቁ እየሰራ መሆኑን እና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጋራ የግብ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.