ዜና፡ ሂውማን ብሪጅ ግብረሰናይ ድርጅት ለወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ

ጥር 04/2015 ዓ.ም ፦ ሂውማን ብሪጅ ግብረሰናይ ድርጅት በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ፡፡

የጤናው ዘርፍ በግጭቱ ከፍተኛ ውድመት ያሰተናገደ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴዔታ ዶ/ር አየለ ተሾመ የተደረገው ድጋፍ ያጋጠሙትን ችግሮች በመቅረፍ የተሟላ የኦፕራሲዮን፣ የምርመራ እንዲሁም ለጨቅላ ህፃናት አገልግሎት በተሟላ ለመስጠት እንዲችል እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚደገፍ መሆኑን በመግለጽ ስለተደረገው ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር እና በተቋሙ አገልግሎት በሚያገኙ ማህበረሰቦች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱል ከሪም መንግስቱ በበኩላቸው ከግጭቱ መቆም በኋላ መሰረታዊ የሚባሉ የጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከር በሚደረገው ርብርብ ተሳትፎ እያደረጉ ለሚገኙት እንዲሁም ለወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ላደረገዉ ለሂውማን ብሪጅ ግብረሰናይ ድርጅት፣ መሳሪዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ የትራንስፓርት ወጪ ለሸፈኑ ለወልድያ ዩኒቨርስቲ እና በሰሜን ካሊፎርኒያ ለአቤኔዘር ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል።

ድጋፉን ያስረከቡት የሂውማን ብሪጅ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር አዳሙ አንለይ ዛሬ ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለሌሎች ጉዳት ለደረሰባቸዉ ተቋማት ከዚህ ቀደምም ድጋፎችን እንዳደረገ ጠቁመው ወደ ፊትም ቀጣይ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና 5 ኮንቴነር የህክምና መሳሪያዎች እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

በርክክብ መድረኩ ላይ የወልድያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት፣ የሰሜን ወሎ ዞን አመራሮች እንዲሁም የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራሮች ተገኝተዋል።

ይህ መረጃ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ ነው።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.