አዲስ አበባ፣ሀምሌ 5፣ 2014 ዓ.ም፡- ሀምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም የወጣውን የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ተከትሎ በተደረገ የኦዲት ሥራ በባንክ የተላከው እና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነቶች ያለው መሆኑንና ላልቆጠቡ ሰዎች እጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች መከሰታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር አስታወቀ፡፡
ከዚህ በመነሳትም “የቤት ማስተላለፉን ሂደት ግልፅነት ለማስፈን ሲባል እና ውጤቱን የሚያዛባ ተግባር ሲያጋጥም መልሰን ኦዲት እንዲደረግ በገባነው ቃል መሰረት የተፈጠረውን ችግር ከጉዳዩ ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት የማጣራት ስራ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በጉዳዩ የተጠረጠሩ ባለሙያዎች እና አመራር በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል” ብሏል።
ሂደቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለቤት ተመዝጋቢዎችና ለመላው የከተማው ነዋሪ የሚያሳውቅ መሆኑን ገልፆ ተመዝጋቢዎች እንደተለመደው በከፍተኛ ትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስኗል፡፡ ለተፈጠረው ስህተት የከተማ አስተዳደሩ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ባሳለፍነው ሳምንት የ20/80 የ14ኛ ዙር የ40/60 3ኛ ዙር የጋራ መኖርያ ቤት እጣ የ20/80 ባለሶስት መኝታ የጋራ መኖርያ ቤት በእጣ ውስጥ አለመካተቱ አነጋገሪ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይህንንም አስመልክቶ የከተማ መስተዳድሩ ባወጣው መግለጫ በዚህ ዙር ለ20/80 የቤት ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ እጣ የወጣባቸውና የተስተናገዱት የ1997 ተመዛጋቢዎች ብቻ መሆናቸውን ገልፆ የ2005 የ20/80 ተመዝጋቢዎች ግን ከስቱዲዮ ጀምሮ ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ በሙሉ በእጣ ውስጥ አልተካተቱም ብሏል፡፡ መግለጫው የ40/60 የቤት ፕሮግራም ግን በ2005 ዓ.ም ብቁ የሆኑ ሙሉ ለሙሉ በእጣ ተካተው በዚህ ዙር የእጣ አወጣጥ በ40/60 ባለአንድ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ ቤቶች እጣ እንደወጣላቸውም አክሎ የገለፀ ሲሆን በዚህ ዙር ያልተስተናገዱት 1997 ዓ.ም የተመዘገቡ ባለሶስት መኝታ ተመዝጋቢዎች ብቻ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
በ1997 ተመዝጋቢዎች ውስጥ በ20/80 ባለሶስት መኝታ እጣ ሊወጣለት የሚችል ተመዝጋቢ የለም በሚል ቤቶቹን በሚያስተዳድረው ቦርድ ውሳኔ ፕሮግራሙ ከሲስተም ውጪ እንዲሆን ተደርጓል ያለው መግለጫው በዚህም ምክንያት በዚህኛው(በ14ኛ) ዙር እጣ ማስተናገድ ያልተቻለ ሲሆን ከተዘጋ በኋላ ግን ከባንክ የተገኘው መረጃ ቁጠባ ያላቋረጡና ብቁ የሆኑ በመገኘታቸው አስተዳደሩ እነኚህን ተመዝጋቢዎች ምንም እንኳን ፕሮግራሙ በይፋ የተዘጋ ቢሆንም ከባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት በአግባቡ እስከቆጠቡ ድረስ ማስተናገድ ስለሚገባ የ1997 ተመዝጋቢ ለሆኑ ባለሶስት መኝታ ቤቶች በአግባቡ የቆጠቡ አስተዳደሩ በሚያወጣው ፕሮግራም በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ መሆኑን አሳውቋል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ሃምሌ 01 ቀን ባሰፈረችው ዘገባ ክብርት ከንቲባ አዳነች አበቤ 14 ኛዉን የ20/80 እንዲሁም 3ኛ ዙር የ40/60 የመኖሪያ ቤት እጣ የማዉጣት ፕሮግራም ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር፤ የአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የቤት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸው እንደነበር መናገሯ ይታወሳል፡፡
በዕለቱም ከንቲባዋ ከ2011 ጀምሮ በግንባታ ላይ የነበሩ ከ139ሺ በላይ ቤቶች ሲሆኑ ከ21.57 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መሰረታዊ ስራዎች በማጠናቀቅ 96.918 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ቁልፍ ለማስረከብ ፣ ከዚህ ውስጥ ለ54ሺ በላይ ባለዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ መደረጉን ገልፀው የቀሩትም መጥተው ቁልፋቸውን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበውም ነበር፡፡ አክለውም ያለዉን ሰፊ የቤት ፍላጎት ለማሟላት አዲስ እይታ መኖሩን የገለጹት ከንቲባ አዳነች የመኖሪያ ኅብረት ስራ፣ በመንግስትና በባለሀብቶች ትብብር፣ በሽርክና ፣በሪል ኢስቴት ፣ እንዱሁም በግለሰብ ደረጃ በሚከናወን የቤት ባለቤትነት የከተማዋን የቤት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ እንደሆነ ማውሳታቸውም የቅርብ ቀን ትውስታ ነው፡፡
የዕጣው ስነ ስራዓትም በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈበት ወቅት ሂደቱ በቴክኖሎጂው የተደገፈ መሆኑ የተነገረ ሲሆነ፤ አጠቃላይ የቤት ፈላጊዎችን መረጃና ለዕጣ የተዘጋጁ ቤቶችን መረጃ ይይዛል፣ ዕጣ ሲወጣ በቀጥታ የአሸናፊዎችን ሙሉ መረጃ እና የቤት መረጃ እንደሚያሳይ፣ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ የአሸናፊዎችና የቤታቸውን መረጃ ያለ ሰው ንክኪ በቀጥታ እንደሚያሳይና ለህትመትም እንደሚያዘጋጅ የተነገረ ሲሆን የተዘረጋው ሲስተም ማንም እንደፈለገ ገብቶ ማስተካከል እና ሌላ ሰው መጨመርም መቀነስም (Edit) ማድረግ የሚከልክል ነውም ተብሎ ነበር። በተቃራኒው ሂደቱን በመቆጣጠር (Audit) ደግሞ ስርዓቱን ራሱ ከህገወጥ ድርጊቶች የሚጠብቅ ሲሆን አንዴ እጣው ከወጣ በኋላ ለሌላ ንክኪ እንዳይጋለጥ ራሱን ዝግ የሚያደርግ ሲስተም መሆኑም ነበር የተገለፀው፡፡አስ