ሰኔ13 ቀን፣2014 ዓ.ም፣አዲስአበባ፦ባለፈው አንድ ወር በአማራ ክልል በተካሄደ የሕግ ማስከበር እርምጃ ከ12 ሺህ 400 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መግለፁን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ዘገበ።
“በፋኖ ስም የሚነግዱ እና በተለያዩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ተደራጅተው በግድያ፣ በዝርፊያ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ “ከአሸባሪ ቡድኖች” ጋር ተልዕኮ ወስደው የክልሉን ሰላም በማናጋት ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ12 ሺህ 400 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እና የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በተመለከት ግምገማ እያደረገ ባለበት መድረክ ሲሆን በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከልም 3 ሺህ 746 የሚኾኑት የመከላከያ፣ የልዩ ኀይል እና በመደበኛ ፖሊስ አባላት የነበሩ ሲኾን ከ8 ሺህ 700 በላይ የሚኾኑት ደግሞ ከፀጥታ መዋቅር ውጭ የኾኑና በልዩ ልዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ክልሉ ላይ ከሕገወጥ ተኩስ ጀምሮ በርካታ ወንጀሎች መቀነሳቸውን ጠቅሰው አበረታች የሰላም ለውጥ ታይቷል ብለዋል
በሕግ ማስከበር ርምጃው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከልም ከ3 ሺህ 750 በላይ የሚኾኑት በዋስ እና በመሰል የማጣራት ሥራ የተለቀቁ መኾናቸው ተገልጿል። በኬላ በተደረገ ቁጥጥር እና ፍተሻም ለህወሃት ሊተላለፍ በመዘጋጀት ላይ ተብሎ ይታሰብ የነበረ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሏል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ክልሉ ላይ ከሕገወጥ ተኩስ ጀምሮ በርካታ ወንጀሎች መቀነሳቸውን ጠቅሰው አበረታች የሰላም ለውጥ ታይቷል ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ የሕዝብን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሕግ ማስከበር እርምጃው መተግበሩ የሚያበረታታ መኾኑን ጠቅሰው በተለያዩ የፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች አያያዝን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተዘዋውረው የሚመለከቱ እና በቀጣይ ግብረ መልስ እንደሚሰጡ ገልፀዋል።አስ