መልእክት ከመቀሌ: ከበባ ውስጥ ባለችው ትግራይ የሴቶች ፈተና

በምሕረት ዕቑባይ በርሀ @MehretOkubay

መቀሌ –  “ጥቅምት 2014 እኩለ ሌሊት ላይ በመቀሌ ሰፈራችን ጩኸት ይሰማል። ጠብ የተፈጠረ መስሎኝ ነበር።  እኔ እና እናቴ ቦታው ስንደርስ ከስድስት በላይ የሚሆኑ ጎረቤቶቻችን በርከት ብለው በአንዲት ሴት  ጩኸት የተነሳ ፊታቸው ላይ ፍርሃት አጥልቶ አየን። በዛችው ሰዓት በጨለማ ፣ በብርድ እና  ቅዝቃዜ ውስጥ – አንዲት ሴት የመጀመሪያ ልጇን እየወለደች ነበር፡፡

እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችሁ  እህቶች ወይም እኛ (አጠገቧ ያለነው) ለምን ስልክ በመደወል አምቡላንስ መጥራት እንዳቃተን ወይም መኪና አስነስተን ወደ ሆስፒታል ለመወሰድ እንደተሳነን ትጠይቁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ትግራይ ለሦስት ወራት ያህል ከበባ ውስጥ ነበረች። ለአብዛኛው ሰው የግንኙነት መቋረጥ የበይነመረብ መዘጋትን ያመለክት ይሆናል። የትግራይ ህዝብ ግን ለብዙ ወራት ያለ የስልክ አገልግሎት እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች እየኖረ ይገኛል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ነዳጅ፣ የባንክ አገልግሎት፣ የእርዳታ እና የህክምና አቅርቦቶች ወደ ትግራይ እንዳይደርሱ ተደርገዋል።

በ2011 አ.ም በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የተካሄደው  አነስተኛ የስነ ህዝብ እና ጤና ዳሰሳ እንዳመለከተው በትግራይ 94 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች ቢያንስ አንድ ጊዜ ለቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ሲያገኙ ፣በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች 81 በመቶ የሚሆኑ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እና 73 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በ7 ቀናት ውስጥ የድህረ ወሊድ አገልግሎት እያገኙ እንደነበር ያሳያል።  በያዝነው ዓመት ግን በትግራይ ጤና ጥበቃ ቢሮ የቀረበው ሪፖረት እነዚ አሃዞች  ወደ 16 በመቶ፣ 21 በመቶ እና 19 በመቶ መቀነሱን ያሳያል።

ይህ የሆነውም በዋናነት የትግራይ የጤና ተቋማት በመውደማቸው ነው። ድንበር የለሽ ሐኪሞች ከታህሳስ 2020 እስከ መጋቢት 2021 በትግራይ  አካባቢዎች ባሉት 106 የጤና ተቋማት ባደረገው ግምገማ 73 በመቶ የጤና ተቋማት የወደሙ ወይም የተዘረፉ ሲሆን 65 በመቶው ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውን ያሳያል።

የትግራይ የጤና ስርዓት ልክ እንደ አብዛኛው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ሁሉ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት አቅርቦት ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም በግዛቱ ውስጥ በሚገኙ ገጠር እና ሩቅ አካባቢዎች አነስተኛ ነገር ግን በርካታ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት እንዲኖር አድርጓል። እነዚህ ተቋማት፣ ለእርዳታ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች ያላቸው ተደራሽነት ያነሰ ቢሆንም፣ በዋናነት የውድመት እና ዘረፋ ሰለባዎች ነበሩ።

የጤና ተቋማት ውድመት በሴቶች የፆታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የማግኘት አቅም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምናልባትም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሴቶችን ስነ ተዋልዶ መብቶች ለመቀልበስ ከተደረጉት ጥረቶች አንዱ ነው

በትግራይ የጤና ተቋማት መውደማቸው ሆን ተብሎ በሴቶች የሚመራውን ዘርፍ ለማውደም ማነጣጠሩን ያሳያል። በትግራይ ከ60 በመቶ በላይ የጤና ባለሙያዎች ሴቶች ናቸው። ይህ የሆነው በከፊል የፆታዊ እና የስነ-ተዋልዶ ጤናን ለማሻሻል የትግራይ ክልል ፖሊሲን ያካተተ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብርን ጨምሮ የሁለተኛ ደረጃ ዲፕሎማ ያላቸው ሴት የጤና ባለሙያዎች በገጠር ቤት ለቤት እየሄዱ በነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች ላይ የስነ ተዋልዶ ጤናን ለማሳደግ በመደረጉ ነው።

ባሁኑ ወቅት የትግራይ ጤና ስርዓት በተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች እና በከተሞች ውስጥ በሚገኙ የጤና ተቋማት ብዛት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ አብዛኞቹ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። አብዛኛዎቹ ፋርማሲዎች ተዘግተዋል፣ ሆስፒታሎች ጓንት እንኳን ሳይቀር በድጋሜ ጥቅም ላይ ለማዋል ተገደዋል፡፡ ብዙ ሆስፒታሎች አስፈላጊ ኬሚካሎች እና መሳሪያዎች ስለሌላቸው የላብራቶሪ አገልግሎቶችን አቁመዋል። እንደ ሂሞግሎቢን ደረጃ ወይም ኮቪድ 19 ፣ የኤችአይቪ ወይም ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን  ላቦራቶሪዎች መመርመር አልቻሉም።

የጤና ተቋማት ውድመት በሴቶች የፆታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የማግኘት አቅም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምናልባትም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሴቶችን ስነ ተዋልዶ መብቶች ለመቀልበስ ከተደረጉት ጥረቶች አንዱ ነው።

የመገናኛ  እና የባንክ አገልግሎቶች መቋረጥ

በዩክሬን የኢንተርኔት አገልግሎት ከመቋረጡ በፊትም እንኳ – ስፔስ ኤክስ  ዩክሬናውያን ከዓለም ጋር እንዳይቆራረጡ  የሳተላይት አገልግሎት ለማቅረብ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። በአንፃሩ ትግራይ ላለፉት 9 ወራት ምንም አይነት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አጥታ የነበረች ሲሆን ከዛ በፊት ደሞ በነበሩት ስምንት ወራት ውስጥ በከፊል እና በመቆራረጥ ብቻ አገልግሎት ታገኝ ነበር። በጦረነቱ የተነሳ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠው ኢንተርኔት አሁን 18ኛ ወሩን ይስቆጥራል።

የእነዚህ አገልግሎቶች መቋረጥ በትግራይ ያሉ ባንኮች የደንበኞችን መረጃ ማግኘትም ሆነ ማዘመን እንዳይችሉ አድርጓል። ይህ የሆነው በትግራይ የተከፈቱ ሒሳቦች በሙሉ  ለወራት በኢትዮጵያ መንግስት ከተጣለው እገዳ በተጨማሪ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ የሚወጡ መረጃዎችን ለማፈን ያደረገው ሙከራ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የመንግስት ወታደሮች ከመቐለ ለቀው ሲወጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የመገናኛ መሳሪያዎችን ዘርፈዉ ነበር የወጡት። መቀመጫቸውን ትግራይ ያደረጉ የቴሌቪዥን ማሰራጫዎችና በክልሉ መንግስት የሚተዳደረውን የትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ጨምሮ  ያደረሱትን ውድመት አይዘነጋም።

በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት አንዲት ሴት ለመውለድ ከመረጠች ወይም ከተገደደች ለቅድመ ወሊድ እንክብካቤ አስፈላጊ የሆኑትን ቪታሚኖች የማታገኝ ሲሆን ፣ የጤና ተቋማት ምጥ ላይ ላሉ ሴቶች ተገቢውን እንክብካቤ የመስጠት አቅም የላቸውም

የቴሌኮሙኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎት መቋረጥ በሴቶች የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ግልፅ የሆነ አንድምታ ያለው ሲሆን ብዙ ሴቶች በገንዘብ ምክንያት ህክምና ሳይደረግላቸው ወይም የጤና ባለሙያዎችን በወቅቱ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይህ ማለት የእርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ መንግስት በአካባቢው ላይ ያለውን ፍላጎት መከታተል እና ምላሽ መስጠት አይችሉም ማለት ነው።  የመሠረታዊ አገልግሎቶች እጦት በሴቶች  ላይ በቤት ውስጥም ችግር ይጨምርባቸዋል። የትግራይ የጤና ማእከላት ህሙማንን መንከባከብ አለመቻላቸው ሴቶች በቤተሰብ ውስጥ የበለጠ ሀላፊነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። የመብራት እጥረት፣ የባንክ አገልግሎት መቋረጥ እና አስፈላጊ ነገሮች በገበያ ላይ አለመገኘት ሴቶች የቤተሰብን ፍላጎት ለማሟላት የበለጠ መስራት እንዲጠበቅባቸው ያደርጋቸዋል።

ምን ቀረ?

በእርግጥ የሴቶችን የስነ ተዋልዶ መብቶች በማረጋገጥ ረገድ ጠቃሚው ነገር የወሊድ መከላከያ መኖሩ ነው። በመቐለ ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች አምስት ፋርማሲዎችን ጎበኘሁ፡፡ አንደኛው የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ እንከብል ነበረው ፣ ሌላው ደግሞ በመርፌ የሚሰጥ የወሊድ መከላከያ ነበረው፣ ከነዚህ ውጪ ሌላ ምንም ነገር የለም፣ ከተለመደው ዋጋ ከሶስት እስከ አራት እጥፍ ይሸጣል። የመጨረሻዎቹ የውርጃ ፒልሰ ትግራይ ውስጥ የሚገኙት  ሰፈሬ በሚገኘው አሰርተሀዴ ለካቲት ሆስፒታል ሲሆን ጊዜው ያለፈበት ከሁለት ወር በፊት ነበር።

በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት አንዲት ሴት ለመውለድ ከመረጠች ወይም ከተገደደች ለቅድመ ወሊድ እንክብካቤ አስፈላጊ የሆኑትን ቪታሚኖች የማታገኝ ሲሆን ፣ የጤና ተቋማት ምጥ ላይ ላሉ ሴቶች ተገቢውን እንክብካቤ የመስጠት አቅም የላቸውም፤ ለጨቅላ ህጻናት ቢሆንም አስፈላጊ የሆኑ ምግቦች አይገኙም ቢገኙ እንኳን ዋጋቸው ውድ ነወ።

እየተካሄደ ያለው ከበባ ሴቶችን ለጾታዊ ጥቃት  ያላቸውን ተጋላጭነት ጨምሯል። በተለይ ሴት ተፈናቃዮች ለአደጋ ተጋልጠዋል። በምዕራብ ትግራይ በተካሄደው የዘር ማፅዳት ዘመቻ በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ምግብ ወይም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማግኘት አልቻሉም። አሁን ሴቶች በግዳጅ ወደ ሴተኛ አዳሪነት እየተገደዱ ነው፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛም አየተካሄደ ነው። በእነዚህ በተጨናነቁ የተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ ለሴቶች እና ህጻናት የመኝታ ኮሪደሮች ባለው እጥረት የተነሳ የሴቶችን ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭነት እንደሚያሳድገው እሙን ነው።

በትግራይ ለሴቶች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማለትም የሳሙና እና ሌሎች መሰረታዊ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እያለቁ ነው።

ወደ ተስፋ

በትግራይ የሚፈጸመውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ይህን ኢ-ሰብአዊነት የሚያረጋግጡ ልዩ ማስረጃዎች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ላይ አንድም ሀገር ወይም አለም አቀፍ ድርጅት ማዕቀብ የጣለ የለም። እንደውም የኖቤል ኮሚቴ በ2019 ለአብይ አህመድ ሽልማቱን ለመስጠት ባደረገው ውሳኔ እንደሚጸና በይፋ አስታውቋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ለሲኤንኤን ዘጋቢ ዘይን አሸር እተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ  ‘ትክክልም ሆነ ስህተት’ አለ ብለው እንደማታምን ገልጻ ግጭቱን – የምግብ፣ የአስገድዶ መድፈር እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን መሳሪያ ያደረገ ‘ውስብስብ’  ግጭት – ስትል ገልጻለች።

ነገር ግን የሊቀመንበሯ መግለጫዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጠቃላይ ውግዘቱን ይዞት የሚመጣውን ሃላፊነት ለመሸሸ የሚደረግ ሲሆን የሆነ ውግዘቶቹ ጥልቀት እና ግልፅነት (በአላማ ረገድም) የሚጎላቸው ነው።

በትግራይ ላለው ቀውስ በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንፃር በአለም ላይ ያለ የጤና ቀውስ ያስከተለውን እጅግ አስከፊ መዘዝ የአለምአቀፉ ማህበረሰቡ ምላሽ  ያስደንቃል። ሆኖም ግን በትግራይ ያለው የጤና ቀውስ ያስከተለውን ጉዳት በክልሉ ውስጥ ሊይዝ እንደሚችል መገመት ካለፈው ክፍለ-ዘመን ዋና ዋና ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር ይቃረናል።  እምነቶቻችን በጣም የተሳሰሩ ናቸው- ለሰብአዊ ጥፋት የሚኖረው ምላሽ ሰብአዊ ብቻ ሳይሆን በጣም ረጅም እድሜ ያስቆጠረውን የሰው ልጅ ጤና እና ደህንነት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው። 

እኔ እና እናቴ ከአልጋችን ተነስተን ከደቂቃዎች በኋላ አንድ ወጣት ሴት በደጃችን ላይ ቆማ ወደ እኔ ዞራ “እባክሽ መቀስ ልታመጪ ትችያለሽ?” አለችኝ። ልጅ ተወለዶ በዚያ ምሽት ሁላችንንም ካሰባሰበን ፍርሃት እና ብስጭት ሌላ ተስፋም ተሰማን- ተስፋ ተሰማን። በምድር ላይ ካሉት ታላላቅ ጅማሮዎች ጋር አብሮ የሚመጣው የተስፋ አይነት ፣ ተስፋ ለተሻለ ወደፊት ፣ ተስፋ ለሰላም ከሁሉ በበለጠ ደሞ ተስፋ ለመልካም ጤንነት።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.