እይታ: በደቡብ ኦሞ ዞን በጸጥታ ሃይሎች እየደረሰ ያለው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ማንነትን እንደ ወንጀል መቁጠር ለዘላቂ ሰላም እንቅፋት እየሆነ ነው

በአስረስ አዲሚ ጊካይ (ዶ/ር)

በደቡብ ኦሞ ዞን የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት

አዲስ አበባ፣ግንቦት 10፣ 2014 – ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አራቱ የአሪ ወረዳዎች የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ብጥብጥ አስተናግደው ነበር። እንደ ዞን የመደራጀት ጥያቄን ተከትሎ በተፈጠረ አለመረጋጋት  በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ከ150 በላይ ቤቶች በእሳት ወድመዋል፣ ሕፃናትን እና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 1000 የሚጠጉ ሰዎች  ተፈናቅለዋል፡፡ ግጭቱ በደቡብ ኦሞ ወደሚገኙ የተለያዩ ከተሞች (ጋዘር፣ መትሰር፣ ሺሺሬ እና ቶልታ) ጨምሮ ተዳርሷል። የአካባቢው፣ የክልሉ እና የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ወደ ብሔር ግጭት ሳይፋፋም ግጭቱን መቆጣጠር ተችሏል። የዞኑን አስተዳደር ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በግጭቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ የዞኑን ዘላቂ ሰላም ለመመለስ እየሰሩ ነው።

ብዙሃኑ የአሪ ህዝብ፣ አዛውንቶች፣ የማህበረሰብ መሪዎች እና ምሁራን ሰላማዊ የፖለቲካ ጥያቄን ተገን  በማድረግ የተወሰኑ የአሪ ወጣቶች  ያደረሱትን  ቃጠሎ፣ ዘረፋ እና የህዝብ ሰላም ማደፍረስ  አውግዘዋል። የአሪ ማህበረሰብ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

መከላከያ ሰራዊት እና የደቡብ ልዩ ፖሊስ አባላትን ያካተተው የጸጥታ ሃይል ሚዛናዊ ፍትህን ማምጣት እና እርቅን ማስፈን ላይ ከማተኮር ይልቅ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽም ቆይቷል። ምንም አይነት የብሔር ግጭት በማይጠበቅበት በደቡብ ኦሞ ዞን የደረሰው የሰብአዊ መብት ረገጣ እና በኮማንድ ፖስቱ እና በደጋፊዎቹ አላማ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

በጎሳ ላይ ያነጣጠረ የማፈን እና መብት የማሳጣት ዘመቻ

ውስን የአሪ ወጣቶች የፈፀሙት የተለያዩ የማቃጠል እና የዘረፋ ወንጀል የአሪን ህዝብ እሴቶች አይወክልም።  የአሪ ማህበረሰብ በደቡብ ኦሞ ከሚገኙ ከ16 በላይ ብሄረሰቦች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰላም ወዳድ ህዝብ ነው። ደቡብ ኦሞ የብዝሃነት፣ የሰላም እና የመረጋጋት አርማ ተደርጎ የሚወሰደው የአሪ ህዝብ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በሰላም አብሮ ለመኖር ባለው ቁርጠኝነት ነው። የአሪ ህዝብ እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎች እና ምሁራን ወንጀሎቹን አውግዘዋል። ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር እየሰሩም ይገኛሉ።

ነገር ግን የአሪ ህዝብ የመረጣቸውን የፖለቲካ ተቋም በሰላማዊና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መንገድ የማደራጀት አቅሙን እስከመጨረሻው ለማሳጣት  እና መብትን ለመንጠቅ  የፖለቲካ አለመረጋጋትን እንደ ምክንያት እየዋለ ነው? ወደዛ የሚያመላክቱ አዝማሚያዎች አሉ።

በመገናኛ ብዙሃን የተደራጀ የስም ማጥፋት እና ማዋከብ ዘመቻ

አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በከተማ እና በገጠር ነዋሪዎች መካከል የሃሰት መከፋፈልን በመቀስቀስ ሰላም ወዳድ እና ታታሪ ግለሰቦች በብሄር ማንነታቸው ምክንያት በስራ ቦታ እንዲንገላቱ ሆኗል።

አንጋፋ የአሪ ማህበረሰብ አባል ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ግለሰቦች ያለ ምንም ማስረጃ በወንጀሉ ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ነው የሚል  የሀሰት ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል። ነጋዴዎች፣ መምህራን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና መምህራንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሪ ወጣቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሁከቱ እጃቸው እንዳለበት የሚያሳዩ አንዳች መረጃዎች ሳይኖሩ ታስረዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የታሰሩት በደቡብ ኦሞ ላይ የሚዘግቡ ማህበራዊ ትስስር ገጾች በአሪ ማህበረሰብ ውስጥ አንጋፋ የሚባሉ ግለሰቦችን ፎቶ መለጠፋቸውን  ተከትሎ ነው። የአሪ ባህል ልብስ መልበስ፣ ለአሪ ዞን (በሰላማዊ መንገድ) መሟገትን እንደ  ወንጀል ማስረጃ ተቆጥሯል። ነገር ግን ከጀርባ ያለው የክሱ ትክክለኛ ምክንያት ማንነት ነው። ለአብነት ያክል፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ ደቆን ጨምሮ ታዋቂ የአሪ ማህበረሰብ አባላት ላይ በርካታ ተከታዮች ባላቸው  እንደ በኢትዮ መሬጃ፣ ኢትዮ ኦሞ እና ሌሎች ሚዲያዎች የተቀናጀ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲደረግባቸው ቆይቷል።

እነዚህ አንዳንድ ጊዜ የፈጠራ መረጃዎችን ለአገር አቀፍ እና ለአለም አቀፍ ተመልካቾች ጋር የሚያቀርቡ ሚዲያዎች የአሪ ህዝብን ለመወንጀል በተቀናጀ መንገድ ይሰራሉ። አብላጫው የማህበረሰብ ክፍል ጥፋተኛ ተብሎ በወል እየተፈረጀ ነው። ከጀርባ ያለው አላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ መሪዎቻቸውን ዝም በማሰኘት ከ400,000 በላይ ህዝብ መብታቸውን መንጠቅ ነው።

በደህንነት ሃይሎች የሚደርስ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ  

በኦሞ ዞን አለመረጋጋቱ ከተፈጠረ በኋላ ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት ባይኖርም የኮማንድ ፖስቱ ጸጥታ ሃይሎች የአሪ ወጣቶችን ያለ አግባብ በማሰር ድብደባ እና እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል።  ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያሉትን እና በጸጥታ ሃይሎች በደረሰባቸው ድብደባ ቆስለው ሆስፒታል የገቡ ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል። ኮሚሽኑ ሪፖርቱን  ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በጸጥታ ሃይሎች በጩቤ/በጦር መሳሪያ  ጫፍ  በደረሰባቸው ድብደባ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ግለሰቦች ቆስለዋል።  ጭንቅላታቸውን ተመትተው ከጆሮአቸው  ውስጥ ለቀናት ደም የፈሰሳቸው፣ ኩላሊት እና ፊኛ በመሳሰሉት  የአካል ክፍሎቻቸው ላይ  የማይድን ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ ናቸው።

ከፀጥታ ሀይሎች እና በአሪ ማህበረሰብ ሙሉ ትብብር  የጸጥታ መደፍረሱን መቆጣጠር እና አጥፊዎችን ተይዞ ለህግ ማቅረብ የተቻለ ቢሆንም፣ የጸጥታ ሃይሎች ይህን የመሰለ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸው የአሪ ማህበረሰብን በዘላቂነት መብት ለመንፈግ እና ለማንበርከክ የሚደረገውን የተቀናጀ ጥረት የሚያሳይ ነው። ይህ ህገ መንግስታዊ ያልሆነ እና ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ በተጨማሪ በዞኑ ውስጥ ባሉ ማህበረሰቦች መካከል ተጨማሪ አለመግባባቶችን ይፈጥራል።

ከላይ የሚታዩት ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን በሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተጠይቀዋል። የሚዲያ አባላት ይህንን ማረጋገጥ ይችላሉ። ነገር ግን የሚታየው አጠቃላይ ካለው ውስጥ አንዱ  አካል ብቻ ነው። 

በርካታ ወጣቶች በእስር ላይ ሳሉ ስቃይ ደርሶባቸዋል፣ ስለሁኔታቸው መረጃ ማግኘት ወደማይቻልበት እስር ቤትም ተዘዋውረዋል። እኔ በግሌ ወደ ዞኑ በሄድኩበት ወቅት እንዳረጋገጥኩት በርካታ ከሁከቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ወጣቶች ተንገላተዋል፣ ታድነዋል፣ ተደብድበዋል።

እኔ እንደ አንድ ራሱን  የአሪ ማህበረሰብ አባል አድርጎ የሚቆጥር ግለሰብ የህዝብን ሰላም ማደፍረስ፣ ቃጠሎ፣ ዘረፋ እና ወንጀልን አውግዛለሁ። በትውልድ ቀዬዬ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትን  ተጎጂዎችን ጎብኝቻለሁ አቅሜ የፈቀደውን ያክል የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ አድርጌያለሁ።

ቢሆንም በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጽመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ማውገዝም የሞራል ግዴታዬ ነው። በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው ጭካኔ ለጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ የሚያደርጉት አካላት በህዝብ ላይ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ‘ሰላማዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ማንሳት  ከፍተኛ መዘዝ ያስከትላል’ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እንደፈለጉ ያሳብቃል። 

ሰላም እና እርቅ ላይ ማተኮር

ኢትዮጵያ በብሔረሰብ፣ በቋንቋ እና በባህል ብዝሃነት  ትታወቃለች።የተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች ያላቸው ከ90 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያም ነች።  ይህ ብዛህነት ባለፉት ዓመታት ማንነትን መሰረት ባደረጉ ግጭቶች መፈጠር ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ፈተና የፈጠረ ቢሆንም፣ እንደ ኦሞ ዞን የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ኃይማኖቶች እና ባህሎች ያላቸው ህዝቦች አብረው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች አሉ። ከነዚህ ቦታዎች መካከል ደቡብ ኦሞ ዞን አንዱ ነው። ባለፉት አመታት በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ሲስተዋሉ ደቡብ ኦሞ ግን ከእንደዚህ አይነት ግጭቶች ነፃ ሆና ቆይታለች።

የዞኑ ነዋሪዎች “የትም ተወለዱ ደቡብ ኦሞ ላይ እደጉ” የሚል ብሒል አላቸው። ይህ  መርህ ያለውን የባህል ብዝሐነት የሚያንፀባርቅ ሲሆን ይህም ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ተቀላቅሎ እንዲኖር ይጋብዛል። በዞኑ የሚገኙ በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአሪ ብሄረሰብ ለዚህ ሰላምና መረጋጋት ዘብ በመቆም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

በሚያዚያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈፀመው ድርጊት ከአሪ ህዝብ እና ከደቡብ ኦሞ ህዝብ የረጅም ጊዜ ባህልና ወግ ጋር የሚጋጭ ነው። ይህንን በመገንዘብ በርካታ ባለድርሻ አካላት የዞኑ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የፌዴራልና የክልል መንግስታት፣ የአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም ዳያስፖራው ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግና ዘላቂ ሰላምን ለመመለስ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ሰላምና መረጋጋትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ፈጣን እርምጃ አስፈላጊ መሆኑ የማይካድ ነው።

ሁሉንም አካታች የእርቅ መንገድ

እርቅና ሰላም ግን ሁሉንም ያሳተፈ መሆን አለበት። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጽንፈኛ እና ፀረ-ሰላም ቡድኖች የአሪ ማህበረሰብን በዘላቂነት የማግለልና ዝም የማሰኘት ስልቶች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ይሸረሽራሉ።

ዘላቂ ሰላምና ስምምነትን ማረጋገጥ የሚቻለው አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብና የህግ የበላይነትን በማስከበር ብቻ ነው። የድህረ ግጭት ህግ ማስከበር እርምጃዎች የህብረተሰቡን የወደፊት አብሮ የመኖር ጉዳይ ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው። በወንጀል የተሳተፉትን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ የችግሩን መንስኤዎች ላይ በመወያየት በጋራ የመኖርና የመበልጸግ መንገዶች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። እርቀ ሰላሙና ውይይቱ እውነተኛ፣ ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና አካታች ካልሆነ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውጥረቱን ለጊዜው ቢያረግብ እንጂ መፍትሔ አይሆንም ።

በደቡብ ኦሞ ያለው ሁኔታ ለእርቅና ለሰላም መንገድ ከመክፈት ይልቅ ህዝባዊ ግጭቶችን ወደ መፍጠር ሲያዘነብል  ይታያል። በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸመው ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የአሪ ብሄረሰቦችን ማሰር፣ በብሄረሰቡ ታዋቂ ሰዎች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ ብሄረሰቡ በአጠቃላይ ጽንፈኛና ዘረኛ አድርጎ መግለጽ እና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር የሞከሩ ሰዎችን ማስፈራራት ምንም ዓይነት ጥቅም አይኖረውም።

ለፌዴራል፣ ለክልላዊ እና ለዞን መንግስታት 

በደቡብ ኦሞ ላለው ተግዳሮት መፍትሄው ሁሉን አቀፍ ውይይት እና እርቅ ነው። ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚከተሉትን ስድስት አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። እነዚህን እርምጃዎች በማስተባበር ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ መንግሥት ንቁ ሚና መጫወት አለበት።

በመጀመሪያ ደረጃ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቱ አላማውን ስላሳካ እና ከዚ በላይ አስፈላጊ ስላልሆነ ስራው መቋረጥ አለበት። ኮማንድ ፖስቱ ከጅምሩ ሁከትና ብጥብጥ በመከላከል ህብረተሰቡን በመጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ተልእኮውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ በዞኑ ሰላምና ማህበራዊ ትስስር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች  ላይ ይገኛል። በዞኑ ሰላም ሰፍኗል፣ ምንም አይነት ተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ የሚታይበት የወታደራዊ ኮማንድ ፖስት መገኘት ከስራ ውጪ እንዲሆን አድርጎታል።

ሁለተኛ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥላቻንና መለያየትን ከመፍጠር መቆጠብ አለባቸው። ለደቡብ ኦሞ ህዝብ የሚያስቡ ሰዎች በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል ድልድይ ከማጥፋት ይልቅ መካከል መገንባት አለባቸው። በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተደብቀው ለህብረተሰቡ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ግለሰቦችን ስም ማጠልሸት በህብረተሰቡ ዘንድ ሊወገዝ ይገባል።  በውይይቱ እና እርቅ ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ግለሰቦች ከሂደቱ እንዲገለሉ ማድረግ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ይጎዳል። ለዚያም መንግሥት አፍራሽ ተዋናዮችን ለይተው እንዲታወቁ በማድረግ እና የሀሰት መረጃ እና የስም ማጥፋት ዘመቻው እንዲጋለጥ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

ሶስተኛ፡ ብሄርን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እና ቅስቀሳዎች በህብረተሰቡ ውድቅ መደረግና እና መሰል ዘመቻዎችን ለመግታት መንግስት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት አለበት።

አራተኛ፡ የተማሩና ተሰሚነት ያላቸውን አመራሮች በተደራጀ መንገድ በማሰር የአሪ ማህበረሰብን ከሰላሙ ሂደት የማግለል አዝማሚያ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።

አምስተኛ፡ መንግስት አስቸኳይ ሁሉንም ያሳተፈ፣ ግልፅ እና እውነተኛ የውይይት መድረክ መፍጠር አለበት።

ስድስተኛ፡ ወንጀሉን የፈፀሙ አካላት በህብረተሰቡና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር  ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።

በደቡብ ኦሞ ያለው ተግዳሮት በሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየታየ ካለው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው። ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመቃወም በአንድነት በቆመ ማህበረሰብ ውስጥ የሰላም እጦት እምብዛም አይስተዋልም። ነገር ግን መንግስት በዞኑ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትክክለኛ ውሳኔዎችን በፍጥነት ካልሰጠ፣ ደቡብ ኦሞ ዞንን ከአንገብጋቢ ችግሮች ዝርዝር ተርታ ለመመዝገብ ይገደዳል። አስ


የአርታኢ ማስታወሻ- አስረስ አዲሚ ጊካይ (ዶ/ር)፣ ለንደን ብሩኔል ዩኒቨርሲቲ ለንደን  መምህር ናቸው። በሚከተለው ኢሜይል አድራሻ ሊያገኟቸው ይችላሉ።  Asress.Gikay@brunel.ac.uk 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.