ዜና: የሞጣ እና አካባቢው ማህበረሰብ የዞን ማዕከልነት ጥያቄ አቀረበ

አዲስ አበባ ግንቦት፣ 10፣ 2014 ዓ.ም- በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ የሞጣና አካባቢው ማህበረሰብ ግንቦት 9/ 2014 ዓ.ም. የዞን ማዕከልነት ጥያቄና የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን የሞጣ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዞን ማዕከልነት ጥያቄ ሲቀርብ የነበረ መሆኑንና  የመድረኩ ዓላማም የአካባቢውን ማህበረሰብ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሆኑን ቢሮ በተጨማሪ ገልጿል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ የኮሚቴው ም/ሰብሳቢ ከፋለ ደምል መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጽሁፋቸውም ሞጣ ከተማ ጥንት የተመሰረተችና የብዙ ታሪክ ባለቤት ፣ የምሁራን መፍለቂያ እንዲሁም አጎራባች ወረዳዎች በትርፍ አምራችነቷ የምትታወቅ መሆኗን አውስተው የአካባቢው ማህበረሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ የመልማት ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል። አክለውም የመድረኩ ዓላማም የሕብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ በቅርበት በመፍታት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም በማስፈን የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ከፋለ ከሶስት ዓመት በፊት ክልሉ ያወጣውን የጥናት መረጃ በመጥቀስ ሞጣና አካባቢው በህዝብ ቁጥር ብዛት 1ሚሊየን 322ሽህ 455 በላይ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማቅረብ የሚፈጀው የጊዜና የገንዘብ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ይህን ተገንዝቦ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ዞን ለመሆንም በቂ ሃብት ያለው መሆኑን የገለፁት ም/ሰብሳቢው ጥያቄው ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ሲቀርብ ቢቆይም የክልሉ አመራሮች መቀያየር እና አሁን ባለው የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ምክንያት  ምላሽ ሳያገኝ የቆየ በመሆኑ አስረድተዋል።  አክለውም  ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን   በየደረጃው ከሚመለከተው አካል ጋር  መስራት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

በመድረኩ  የነበሩ ተሳታፊዎች ጥያቄያቸው  የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈታላቸው መሆኑን  ገልጸው የክልሉ መንግስት ችግሩን አይቶ ምላሽ እንዲሲጣቸው ጠይቀዋል።

በመድረኩም የክልል ምክር ቤት ተወካዮች፣ የሞጣና አካባቢው የ6 ወረዳና የ4 ከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ምሁራንና የተውጣጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ እንደነበሩ መረጃው ያመለከተ ሲሆን የቀጣይ አቅጣጫን የሚያስፈጽም ጥምር ኮሚቴ በማቋቋም  ውይይቱ  ተጠናቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.