እለታዊ ዜና – ሸገር ዳቦ በነገው እለት ስርጭቱን እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ተናገሩ

ባዶ ሸገር ዳቦ የችርቻሮ ሱቅ በአዲስ አበባ

አዲስ አበባ የካቲት 30፣ 2014 – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ 613 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ፣ እንዲሁም በ198 ሚሊዮን ብር ለስንዴ አቅርቦት በድምሩ 812 ሚሊዮን ብር በመመደብ የዳቦ ምርት ማስጀመር ችሏል በማለት ተናግረዋል::

“ከነገ ጀምሮም ምርቱ ወደ ገበያ የሚወጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ የሸገር ዳቦ በምናሰራጭባቸው ማዕከላት ዳቦ ማግኘት ይችላል” በማለት ከንቲባ አዳነች ገልፀዋል::

“የከተማችን የንግዱ ማህበረሰብም በመተሳሰብ ለጊዜው ትርፋችሁን ቀንሳችሁ ህዝባችሁን ታተርፋ ዘንድ በአክብሮት ጥሪ እናቀርብላቹሃለን።”

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ከንቲባዋ ፋብሪካው በእድሳትና በወቅቱ የስንዴ ዋጋ ንረት ምክንያት ለጊዜው ማምረት አቁሞ እንደነበር ገልፀዋል:: “እነዚህ ምርቶች ዝቅተኛውንና በተለይም ቅድሚያ ወደሚሰጠው ህዝብ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ ላይ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ቁጥጥር ቢኖርም ነገር ግን ህዝቡ በተለይም የዳቦ በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ እየቀረበ ሳለ የተሻለ ገቢ ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ምርቱን ወስደው የሚያተርፉበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ” በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል:: “ህብረተሰቡ ይህንን ሁኔታ በመጠቆምም፣ በማጋለጥም፣ በመቆጣጠርም በኩል ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ። የከተማችን የንግዱ ማህበረሰብም በመተሳሰብ ለጊዜው ትርፋችሁን ቀንሳችሁ ህዝባችሁን ታተርፋ ዘንድ በአክብሮት ጥሪ እናቀርብላቹሃለን።”

በአዲስ አበባ ከተማ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች በድጎማ መልክ የማያቋርጥ የዳቦ አቅርቦትን ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሸገር መጋገሪያ ከተመረቀ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ምርት በማቆሙ ወዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪወችን ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል።

የኢትዮ-ሳዑዲ ቢሊየነር ሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ንብረት በሆነው በሚድሮክ ኢትዮጵያ በ900 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይህ ዘመናዊ ዳቦ መጋገሪያ በሰኔ 2012 ምረቃ ላይ በተሰራጨ መግለጫ መሠረት በሰዓት 80,000፤ በቀን 1.8 ሚሊዮን ዳቦ ያመርታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ነገር ግን ገና ከተመረቀ በስድስት ወራት ውስጥ  70 ሚሊዮን ብር ከዋጋ ንረት እና ከአቅርቦት እጥረት በተነሳ በተነሳ ኪሳራውን አሳውቆ ነበር። ይሁንና መጋገሪያው ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም የቆሙ የከተማ አውቶቡሶችን ጨምሮ በአዲስ አበባና አካባቢው በሚገኙ ከ400 በላይ የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችን በመጠቀም በቀን ከ700,000 እስከ 800,000 የሚደርሱ ዳቦዎችን በማምረት ምርቱን ለከተማው ነዋሪዎች ሲያከፋፍል ቆይቷል ።

በወቅቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመዲን ሸገር ዳቦ መጋገሪያ ለተጠቃሚዎች እየቀረበ ያለው ዋጋ  ከሚያስፈልገው ግበአት እንዲሁም ለስንዴ ግዥና ለአመራረት ሂደቱ ግብአት ጋር ሲነፃፃር ተመጣጣኝ አልነበረም ሲሉ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.