አዲስ አበባ፣ ህዳር 7/2015 ዓ.ም፡- በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ወባ፣ ኩፍኝ እና ኮሌራ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ በመከሰታቸው ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ቦቶሬ ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ገልጸዋል።
በክልል የኩፍኝ በሽታ በዘጠኝ ዞኖች ማለትም ምስራቅ ባሌ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ጅማ እና ባሌ፣ የተከሰተ ሲሆን የወባ በሽታ ደግሞ በአስራ አንድ ዞኖች እና በአራት ከተሞች ማለትም ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ጅማ፣ ኢሉ አባቦር፣ ምዕራብ አርሲ፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ባቱ፣ ሻሸመኔ፣ ጅማ እና ነቀምቴ ተከስቷል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የኮሌራ በሽታ ደግሞ በባሌ ዞን ውስጥ በወረርሽኝ መልክ መስፋፋታቸው ተገልጿል።
ኃላፊው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር ስርጭት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ የመድሃኒት አቅርቦትና የፀረ ኮሌራ ክትባት ስራ ቢካሄድም የበሽታዎቹን ስርጭት ባለመግታቱ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ ከአንድ አመት በታች ያሉ ህጻናት በየወሩ የኩፍኝ መደበኛ ክትባት እንዲወስዱ፣ ህብረተሰቡ ሽንት ቤት፣ በኬሚካል የታከመ ወይም የፈላ ውሃ እና የበሰለ ምግብ እንዲጠቀም፣ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ስፍራዎችን እንዲያፀዳ፣ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀምና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ፣ እንዲሁም ማህበረሰቡ አጠራጣሪ ምልክቶችን በራሳቸው ወይም በህፃናት ላይ ካዩ በአቅራቢያ በሚገኝ ጤና ጣቢያ በመሄድ ምርመራ እንዲያደርጉ ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።አስ