ትኩስ ዜና፦ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው በ 10 ሺ ብር ዋስትና እንዲወጣ ተፈቀደ

ሰኔ 21፣ 2041 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ የ”አልፋ ሚዲያ ባለቤትንና አዘጋጅ የሆነውን ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውን በ10 ሺ ብር ዋስ ከስር እንዲፈታ ፈቀደ።

“ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት” ወንጀል ተጠርጥሮ ከአንድ ወር በላይ በስር ላይ የነበረው የአልፋ ሚዲያ ባለቤትና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ዛሬ በ10 ሺህ ብር ዋስ ከስር እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።
ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ግንቦት 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፖሊስ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥሬዋለሁ በሚል ቅዳሜ ግንቦት 20፤ 2014 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ክስ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ አክሎም፤ በቃሉ “በተለያዩ በመንግስት ሚዲያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ በማድረግ መንግስት እንዲጠላ እና ሀይማኖታዊ ግጭት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሷል” ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ፍርድ ቤት ያለ ጠበቃ የቀረበው ጋዜጠኛ በቃሉ በበኩሉ “ስራ እንዳልሰራ ተደርጌያለሁ በመንግስት ሚዲያም ቀርቤ አላውቅም” ብሏል። በቃሉ በችሎቱ ላይ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ሲል የተከራከረ ሲሆን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.