ሰኔ29 ቀን፣2014 ዓ.ም፣አዲስአበባ፡-በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በተለምዶ “እሪ በከንቱ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጎጆ ቀልሰው ይኖሩ የነበሩ 80 አባወራዎች “መንግስት ያለተቀያሪ ቤት እና ያለማስጠንቀቂያ ለአመታት ከምንኖርበት ቤት አፈናቅሎ ጎዳና ላይ እንድንወጣ አድርጎናል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።
የ38አመት ጎልማሳ የሆነው ምትኩ ተስፋዬ በወረዳው ተወልዶ እንዳደገ እና በአካባቢው ለሚደረጉ የፀጥታም ሆነ የምርጫ ክዋኔዎች ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳበረከተ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል። “መንግስት ለሀብታም ልጆች መዝናኛ ከጎናችን ሲሰራ እኛን ግን ተስፋ ብቻ እየሰጠ አስቀምጦ ጎዳና ላይ ከነልጆቻችን በትኖናል። አጠገባችን ለሚገኘው ወዳጅነት ፓርክ ለወፍ መኖሪያ ቤት የሚሰራ መንግስት ነው እኛን ዜጎቹን ጎዳና የበተነን” ሲል በሁኔታው እጅግ እንዳዘነ ተናግሯል።
ምትኩ አያይዞም የመንግስት አካላት “ቤት ይሰጣችኋል” እያሉ ተስፋ ይሰጧቸው እንደነበር እና በአመራሮች ተደጋጋሚ መቀያየር ምክንያት ጉዳያቸው ለአመራሮች እንግዳ ጥያቄ ስለሚሆን የሰነቁት ተስፋ እልባት ሳያገኝ የውሃ ሽታ እንደሆነባቸው አስረድቷል። አሁናዊ ሁኔታውን ሲያስረዳም፣ “አሁን መንገድ ዳር ላስቲክ ወጥረን ስናድር ደንቦች እየመጡ ያስፈራሩናል። ከተወለዱ ሁለት ሳምንት የሆናቸውን ጨቅላን ጨምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ በርካታ ህፃናት እዚህ ምቹ ባልሆነ መጠለያ ውስጥ እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ብሏል። አክሎም መንግስት ዜጎቹን እኩል ማየት እንዳለበት አሳስቦ የድሃን ልጆች ወደ ጎዳና አስወጥቶ አካባቢውን ለባለ ሃብት መስጠቱ አግባብ አይደለም ሲል ለዘጋቢያችን ተናግሯል።
የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነች የ18 አመት ሴት ልጅ አለችኝ” ሲል የተናገረው ዳንኤል ሴት ልጁ ላይ “የፆታ ጥቃት” እንዳይደርስባት እጅግ መስጋቱንም አክሎ ገልጿል
አዲስ ስታንዳርድ ካነጋገረቻቸው ምስክሮች ማካከል የ49 ዓመቱ ጎልማሳ ዳንኤል ሀይሌ አንዱ ነው። ዘጋቢያችን እንዳየችው ዳንኤል በላስቲክ ቤት ከባለቤቱ እና ከስምንት የቤተሰብ አባሉ ጋር ተጠልለው ነበር። “ለምርጫ ውጡና ቀስቅሱ፣ ለፀጥታ አካባቢያችሁን ጠብቁ ሲል የነበረ ቀበሌ እና ወረዳ ዛሬ ቤታችንን አፍረሶ እኛን ጎዳና ላይ በትኖናል” ሲል ምሬቱን ገልጿል።
እርሱና ቤተሱቡ እንዲሁም በአካባቢው ለመሰል ችግር የተዳረጉትን የማህበረሰብ ክፍል በቅርብ ርቀት የሚገኘውን የሸገር ፓርክ ፕሮጀክት አስመልክቶ ዳንኤል በንፅፅር ለዘጋቢያችን ሲያስረዳ፣ “በሚሊየን ብር የተገነባ ፕሮጀክት የሸገር ግርጌ ጎዳና ላይ እንገኛለን። በትንሽ እርቀት ሁለት አይነት ህይወት ነው የምታይው” ብሏል።
ዳንኤል አክሎም ባለቤቱ በዘውዲቱ ሆስፒታል 3 መንታ ልጆች ወልዳ የሚዲያ ሽፋን ካገኙ በኋላ ሲኖሩበት ከነበረው በአቅራቢያ “መጥፎ ሽታ” ካለው አካባቢቤት አሁን በቅርብ በመንግስት ሃይሎች ወደተነጠቀው ቤት በወቅቱ የነበረው የወረዳው አስተዳዳሪ የዛሬ ስድስት አመት እንደሰጠው ተናግሯል። “ዛሬ ግን ከነ ልጆቼ ጎዳና ላይ ነኝ። የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነች የ18 አመት ሴት ልጅ አለችኝ” ሲል የተናገረው ዳንኤል ሴት ልጁ ላይ የፆታ ጥቃት እንዳይደርስባት እጅግ መስጋቱንም አክሎ ገልጿል።
“እዚህ መኖር ከጀርኩ 13 አመት አልፎኛል።ወልጄ በተኛሁበት ቤቱን አፈረሱት። አሁን ከነ ልጄ በጣም ከፍተኛ ችግር ላይ ነኝ”
ዝናሽ ስሜነህ
አካባቢው ከ10 አመት በፊት ሲፈርስ እርሱ የት ይኖር እንደነበር እና መንግስት በወቅቱ ለምን ተለዋጭ ቤት እንዳልሰጠው ከአዲስ ስታንዳርድ ለቀረበለት ጥያቄ “ትዳር የዛሬ 22 ዓምት መስርቼ እዚሁ ቀበሎ በሚገኘው እናቴ ግቢ ውስጥ ቤት ሰርቼ እኖር ነበር። አካባቢው ሲፈርስ ለእናቴ ጀሞ ባለ አንድ መኝታ ቤት ተሰጣት። ነገር ግን እኔ በጥገኝተን ስኖር ስለነበር ቀበሌው ተጠባባቂ አደርጎ መዘገበኝ” ሲል ዳንኤል አብራርቷል። አሁን ስላለው ሁኔታም ለዘጋቢያቸን እርሱ ለዘመናት ተመዝግቦ ነገ ቤት ይሰጠኛል ብሎ ቢያስብም ተስፋ ያደረገው ግን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ህልሙ እየመከነ መሄዱን ተናግሯል። “ ከእኔ በኋላ ለመጡ ቤት ይሰጣል። እኔ ግን የምከፍለው ስለሌለኝ እዚሁ ላስቲክ ቤት ውስጥ ነኝ” ሲል በሙስና አንዳንድ የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ቤት በአድሎ እንደሚሰጡ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ከወለደች 15 ቀን የሆናት አራስ ዝናሽ ስሜነህ መኖሪቸው ከፈረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ትገኛለች። “እዚህ መኖር ከጀርኩ 13 አመት አልፎኛል።ወልጄ በተኛሁበት ቤቱን አፈረሱት። አሁን ከነ ልጄ በጣም ከፍተኛ ችግር ላይ ነኝ። ብርድና ፀሀይ እየተፈራረቀብን ነው። እኔስ እችለዋለሁ።ለህፃኑ ግን በጣም ከባድ ነው። መንግስት ትንሽ ቤት እንኳን ቢሰጠኝ” ስትል ተማጽናለች።
የነዋሪዎቹን ችግር መነሻ በማድረግ የወረዳው አስተዳደር ለዜጎች ተለዋጭ ቤት ሳይሰጥ ዜጎችን ማፈናቀሉ በምን አግባብ ነው ስትል የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኛ የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 ምክትል ስራ አስፈጻሚ እና ስራ ፈጠራ ጽህፈት ቤት ኀላፊ የሆኑትን ወ/ሮ ዩዲት ብዙነህን አናግራለች።
“በጣም በሚገርም ሁኔታ ኮንዶሚኒየም ቤት ተሰጥቷቸው እሱን አከራይተው በህገ-ወጥ መንገድ ሸራ ወጥረው እዚህ የሚኖሩ አሉ”
ወ/ሮ ዩዲት ብዙነህ
“ወረዳችን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ህግ የማስከበር ስራ ሰርቷል። ህገ-ወጥ ቤቶችን አፍርሷል” ያሉት ሃላፊዋ አክለውም፣ “በቀድሞ ቀበሌ 15 አሁን ብሎክ 30/32 የሚባለው ቦታ መንግስት ቦታውን ለልማት ስለሚፈልገው የግል እና የቀበሌ ቤቶች እንዲሁም የንግድ ቤቶችን ከስድስት አመት በፊት እንደ አቅማቸው አስተናግደን መሸኛ ሰተን ከወረዳችን ሸኝተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሃላፊዋ አሁን በላስቲክ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው ያሉትን ነዋሪዎች “በህገወጥ መንገድ ሸራ ወጥረው የሚኖሩ” ናቸው ያሉ ሲሆን ወረዳው በተለያየ ጊዜ ቢያስነሳቸውም እንደገና ሸራ ወጥረው መኖር መጀመራቸውን አስረድተዋል። አያይዘውም በፊት ነዋሪ ከነበሩት አንድም ያልተስተናገደ አካል እንደሌለ ተናግረው፣ “በጣም በሚገርም ሁኔታ ኮንዶሚኒየም ቤት ተሰጥቷቸው እሱን አከራይተው በህገ-ወጥ መንገድ ሸራ ወጥረው እዚህ የሚኖሩ አሉ” ብለዋል።
ሃላፊዋ አያይዘውም ህጋዊ መረጃ እያላቸው በአግባቡ ያልተስተናገዱ የህብረተሰብ አካላት ካሉ አሁንም ለማስተናገድ ወረዳው ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፣ አንዳንድ ግለሰቦች ቤት ሲሰጣቸው ልጆቻቸውን ትተው በመሄዳቸው ለተፈጠረው ችግር እንደምክንያትነት አንስተዋል። “አሁን በህግ እና በስርአት እየለየን ነው ያለነው። ህገወጦችን ግን የሚያበረታታ አሰራር የለም” ያሉ ሲሆን አሁን በሸራ ወጥረው የሚኖሩበት ስፍራ የእግረኛ መንገድ ስለሆን ነዋሪዎቹ ለቀው እንዲሄዱ እንደተ ጠየቁ እና ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል። አስ