አዲስ አበባ፣ ጥር 18/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የኦሮምያ ልዩ ዞን ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን መንደሮች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች አስታወቁ። ከተገደሉት መካከል የአከባቢው ታጣቂዎች እና ንጹሃን ዜጎች እንደሚገኙበትም ተገልጿል። የአማራ ክልል መንግስት ትላንት ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ከክልሉ ልዩ ሀይል በተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት በአከባቢው ሰላም አና መረጋጋት ለማስፈን እንዲሰፍሩ መደረጉን አመላክቷል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ቀን በተነሳው ግጭት በርካታ ቤቶት መቃጠላቸውን፣ ንብረቶች መዘረፋቸው ያስታወቁት ነዋሪዎቹ ግጭቱ በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን ከተሞች ተዛምቷል ብለዋል። ግጭቱ ከተዛመተባቸው ከተሞች ውስጥ ሸዋሮቢት፤ አጣየ፤ ኤፍራታ ግድም ወረዳ ጃዋ ከተሞች ተጠቅሰዋል።
በሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳዳር የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ትላንት ባወጫው መግለጫ የህዝቡንና የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ከጥር 17 ቀን ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ በከተማዋ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡
መግለጫው የከተማው ማህበረሰብ ፣ የጸጥታ አካላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የከተማዋን ሰላማዊ እንቅስቅሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።
“ባይሳካላቸውም ጥላቶቻችን በመካከላችን አንድነትና ትብብር እንዳይኖር በርካታ የሴራ ድግሶችን ደግሰው ለማራራቅ ሞክረዋል” ያለው የከተማ አስተዳደሩ የአማራ ህዝብ ህልውና አደጋ የሆኑ ወረራዎችን ለመከላከል ብሎም አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ህይወታቸውን ላጡ ሀይሎች የተሰማውን ሀዘን ገልጧል፡፡
በአማራ ክልል መንግስት በወጣው መግለጫ ግጭቱ የተቀሰቀሰው በኤፍራታና ግድም ወረዳ ጃዋ ቀበሌ በሚገኝ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እና ፌደራል ፖሊስ አባላት በሚገኙበት ካምፕ ላይ ጸረሰላም ያላቸው ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት መሆኑን አመላክቷል። በክልሉ መንግስት መግለጫ ላይ ጸረ ሰላም ሀይሎች ሲል የገለጻቸው አካላት ከካምፑ በተጨማሪ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይም ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል።
ነገር ግን የሰንበቴ ከተማ ነዋሪዎች ከባባድ መሳርያዎችን ታጥቀው የሚጓዙ የአካባቢው ታጣቂዎች ቅዳሜ ጥር 13፣ 2015 ዓ.ም. በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡
“የሚይዙት መሳርያ ዲሽቃ(የሩሲያ ሰራሽ መሳርያ) የሚባለውን ነው፤ የአርሶ አደሮችን ቦቶች እና ንብረቶቻቸውን በዚህ መሳርያ ነው ያቃጠሉት፡፡ ሰላማዊ ሰዎችን ይገድላሉ፡፡ በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በሚገኙ ሁሉም ከተሞችና ቀበሌዎች በማል በሚቻል ደረጃ ይህንን ተግባር እየከወኑ ነው” በማለት ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ አንድ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡
የነዋሪው ቅዳሜ እለት የጀመረው ጥቃት እስከ ማክሰኞ ድርስ በመቀጠሉ በርካቶች መሞታቸውንና ነዋሪዎቹ ከቀያቸው እንዲሰደዱ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
“በአሁኑ ሰዓት ጫካ ውስጥ ነው ተደብቀን ያለነው፡፡ የመንግስት ሀይሎች መጥተው እንዲሚያተርፉን ተስፋ አድርገን የነበረ ቢሆንም ይህ አልተቻለም፡፡ ሶስት ቀን ሆኖናል፣የምንበላው ምንም ነገር የለንም፡፡ የፀጥታ ሁኔታው አስፈሪ በመሆኑ እና ትርንስፖርት ባለመኖሩ ወደ ሰላማዊ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻለንም፡፡” ሲል ማክሰኞ እለት ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጧል፡፡
ነዋሪው አክሎ እንደገለፀው ጥቃት ፈፃሞዎቹ ፋኖ በመባል የሚታወቁትና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ሌላኛው ነዋሪ ግን ታጣቂዎቹ ንብረትነቱ የልዩ ሀይሉ የሆነ ከባባድ መሳርያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ መሆንን ገልፆ በክልሉ መንግስት ተሸከርካሪ ሲጓዙ እንደነበር ተናግሯል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ ጥቃቱን በመሸሽ ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱት ሁሉም ዜጎች ለቀናት ያለ ምግብና መጠጥ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ናቸው፡፡
የጅሌ ጥሙጋ ኮሙኑኬሽን ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ “ሰንበቴ ከተማ በአሁኑ ሰአት ጭንቅ ውስጥ ገብታለች፡፡ ዱኣ ወይም ፀሎት ትፈልጋለች፡፡ የሚመለከተው የመንግስት ባለድርሻ አካላትንም ልዩ ትኩረት ትሻለች።” በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከነዋሪዎቹ ከተናገሩት እና አንዳነድ ሚዲያዎች በጥቃቱ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ተሳትፎ ከገለፁት በተቃራኒ የአማራ ክልል መንግስት ሃይሎቹን በስፋት ባይጠቅስም “ፀረ ሰላም ሀይሎች” ሲል ወቅሷል፡፡ አክሎም በጥቃቱ ንፁሃን ዜጎችና የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ አንዚህ የፀረ ሰላም ሀይሎች የብሔር መልክ ያለው እንዲመስል በማድረግ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን እያደረጉ እንደሆኑ አክሎ ገልጧል፡፡
የኦሮሞ ልዩ ዞን አስተዳዳሪ አህመድ አሊዪ ለቢቢኢ አፋን ኦሮሞ እንደገለፁት ጥታቱ የተጀመረው ሰኞ እለት በአካባቢው ወጣቶችና እና በልዩ ሃይሉ አባላት መካከል በነበረ አለመግባባት መሆኑንና በዚህም የተነሳ ሰባት የኦሮሞ ወጣቶች በልዩ ሃይሉ መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም በኋላ ላይ በአከባቢው ነዋሪዎችና በክልሉ ልዩ ሀይል መካከል ግጭት እነድዲቀሰቀስ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
አህመድ ማቾቹ ያልተለዩ መሆናቸውንና የልዩ ሃይሉ አባላት እና ንፁሃን ሰዎች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ “ የማቾቹን ቁጥር እስካሁን አልታወቀም፣ ግን በርካታ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በርካታ ቀበሌዎች ተቃጥለዋል” በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በተፈጠረው ጥቃት የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይልንና ፋኖ በመባል የሚታወቀውን ኢ-መደበኛ ታጣቂን ተጤቂ ያደረገ ሲሆን ከቅዳሜ ጀምሮ የተገደሉት ንፁሃን ቁጥር ከ68 በላይ እነደሆነ ገልጧል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ( አብን) በበኩሉ ትላንት ባወጣው መግለጫ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሰርገው በገቡ አካላት ጭምር የሚደገፉ ኃይሎች በልዩ ኃይል እና በፌደራል ፖሊስ ሀይል ላይ ጥቃት በመፈፀም ሳይገቱ በአካባቢው ንፁሃን ነዋሪዎች ሳይቀር ከፍተኛ ጥቃት እየፈፀሙ ይገኛሉ ሲል ተሷል::
አብን አክሎም የአማራ ክልል መንግስት አፋጣኝ እና ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ ከፍተኛ ውድመት እና እልቂት እየደረሰ ይገኛል ሲል የክልሉን መንግስት ወቅሷል፡፡
በተደጋጋሚ ለሚፈጠረው ግጭት መጋለጥ
የኦሮሞ ልዩ ዞን እና አዋሳኝ የሰሜን ሸዋ ዞን በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ግጭት የተጋለጠ ነው፡፡ የአካባቢው በለስልጣናት እነደሚገልፁት ባሳለፍነው አመት ሐምሌ ወር 17 ንፁሃን ተገድለዋል፣ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል እንዲሁም ንብረቶቻቸው ወድሟል፣ ቤታቸው ተቃጥለሏል ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በተመሳሳይ አመት ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ በሚያዚያ ወር አዲስ ስታንዳርድ በአከባቢው ሰላማዊ ሰዎች በፋኖ ሃይል በአሰቃቂ ጥቃት መገደላቸውን እንዲሁም በርካቶች በሸዋ ሮቢት እና ወሰን ቁረቁር መካከል በምትገኝ ኮላሽ ወደሚባል ቦታ መፈናቀላቸውን ዘግባለች፡፡
ሚያዚያ 2021 በዚያኑ ቦታ አውዳሚ ጥቃት የነበረ ሲሆን በጥቃቱም በርካታ ሰዎች ሞተዋል፣ ቢያንስ 358 ሺ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ የግጭት መእከል የሆነችው አጣዬ ከተማ ሙሉ ህዝብ ከቀየው ተፈናቅሎ ከተማዋ ተቃጥላለች ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም በሪፖርቱ የአማራ ክልል መንግስት ኦሮሞ ልዩ ዞን እና በሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ግጭት የሚጠበቅበት ማድረግ አለመቻሉን ገልጧል፡፡ ተቋሙ በሚያዚያ ወር ላይ በነበረው ግጭት ላይ በተደረገው ምንመራ 303 ሰዎች መሞታቸውን፣ 369 መቁሰላቸውን፣1539 ቤቶች መቃጠላቸውንና ከሁለቱ ዞኖች አስተዳደሮች በተገኘው መረጃ መሰረት ከ50ሺ ሰዎች በላይ መፈናቀላቸውን ገልጧል፡፡ የእርዳታ አቅርቦት የቀጠለ ሲሆን የሰሜን ሸዋ ዞን ከኦሮሞ ልዩ ዞን የተሸለ ቢሆንም በሁለቱም ዞኖች አቅርቦቱ በቂ አለመሆኑን ጨምሮ አስታውቋል፡፡አስ