ዜና፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አዲሱ የመደበኛና የልዩ ሀይል የደንብ ልብስ ይፋ ሆነ፥ ከዛሬ ጀምሮም በስራ ላይ ይውላል

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመደበኛና የልዩ ሀይል የደንብ ልብሶች

አዲስ አበባ፣ጥር 18/ 2015 ዓ.ም፡– አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመደበኛና የልዩ ሀይል የደንብ ልብሶች በዛሬው እለት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ይፋ ሆኗል። የደንብ ልብሶችም ከዛሬ ጀምሮ በስራ ላይ መዋል ይጀምራሉ ተብሏል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳለው በአዲስ መልክ የተቀየረውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የደንብ ልብስ አስመልክቶ የስራ መመሪያ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተቋሙ ከሰራቸው በርካታ የለውጥ ስራዎች ውስጥ ይህ አዲሱ ዩኒፎርም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የአሁኑ አዲሱ የደንብ ልብስ የተቋሙንም ሆነ የሠራዊቱን ክብር የሚመጥን በመሆኑ በየትኛውም የስራ ቦታ የተቋሙን፣የሠራዊቱን፣ ስም፣ዝናና ክብር በሚመጥን መንገድ መገልገል እንደሚገባም አሳስበዋል ።

በሠራዊቱ የሚጠየቁት የመብት ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት በሂደት ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።

“የደንብ ልብሱን በአዲስ መቀየር ያስፈለገበት ምክንያት በቀድሞው ደቡብ ክልል የነበረው የደንብ ልብስ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት በመስጠቱና የተቋሙንም ሆነ የሠራዊቱን ክብር የሚገነባ ሆኖ ባለመገኘቱ እንደሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳይያስ ገልጸዋል” ሲል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።

ባለፈው አንድ ዓመት በኮሚሽኑ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እንደተሰሩ የገለጹት ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳይያስ በተለይ በሰራዊቱ የሰው ሃይል ግንባታ ላይ የተለያዩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። አዲሱን የደንብ ልብስ ( ዩኒፎርም ) ከሠራዊቱ ውጭ ሌላ ለብሶ የሚገኝ ከሆነ በህግ ያስጠይቃል ብለዋል ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.